በወረቀት ብር ላይ ሪባ (ወለድ/ አራጣ) አለ?

Home የፈትዋ ገጽ ገንዘብ ነክ በወረቀት ብር ላይ ሪባ (ወለድ/ አራጣ) አለ?

ጥያቄ፡- አበዳሪ ከተበዳሪ የሚያገኘውን ኢንተረስት ወይም ወለድን አስመልክቶ አንዳንድ ውዝግቦች ይነሳሉ። አንድ ሰው አንድ ሺህ ብር ያበድርና በውል በታወቀው ጊዜ ላይ ሲመልስ አንድ ሺህ አንድ መቶ ወይም አንድ ሺህ ሁለት መቶ አድርጎ ለአበዳሪው ይመልሳል። ውሉ የተካሄደው ደግሞ በወረቀት ገንዘብ ነው። አንዳንድ ሰዎች እንዲህ ዓይነቱ ውል ሪባ/አራጣ እንዳልሆነ ያምናሉ። በወርቅና በብር (ሲልቨር) እስካልሆነ አራጣ/ሪባ የለም ባዮች ናቸው። እነዚህ ሁለቱ መገበያያዎች በቀድሞው ዘመን እንደመገበያያ ገንዘብ ይጠቅሙ እንደነበር ይታወቃል።  ስለዚህ እንደ ሰዎቹ እምነት በአሁኑ ዘመን የመገበያያ አገልግሎት የሚሰጠው የወረቀት ገንዘብ ላይ ሪባ/አራጣ የለም። በወርቅና በብር ላይ ብቻ ነው ወለድ ያለው። በወርቅና በብር ላይ ግን በጊዜ ገደብ እየጨመረ የሚመጣን ብድር ማበደር እርም ነው ብለው ያምናሉ። እነዚህ ሰዎች አሁን ያለው የወረቀት ገንዘብ በአላህ መልእክተኛ ዘመን አለመኖሩን እንደማስረጃ ይጠቀማሉ። ስለዚህ እንደነርሱ አባባል የሪባ/የወለድ እርምነት የወረቀት ገንዘብን አላጠቃለለም ባይ ናቸው። ነገርግን ሌሎች የምናውቃቸው ብዙ ዑለሞች በወርቅና በብር መገበያየትና በወረቀት ገንዘብ መገበያየት አይለያይም ይላሉ። የወረቀት ገንዘብ የብርና የወርቅን ገንዘብ ተክቶ ይሰራል ባይ ናቸው። በዚህ ዘመን እንደመገበያያ እስካገለገለ ድረስ እንደ ወርቅና እንደ ብር ይታያል። ስለዚህ በርሱ ላይ ወለድ/አራጣ ማሰብ ሐራም ነው ይላሉ። ከነዚህ ሁለት ሃሳቦች የትኛው ይሆን ትክክል? በሸሪዓዊ ማስረጃዎች የተደገፈው አቋም የቱ ነው?


መልስ፡- በዚህ ጉዳይ ላይ ታላቁ የዘመናችን ዓሊም የዐለም ዑለማኦች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት እና ተቀዳሚው የለውጥ አራማጅ ዓሊም ዶክተር ዩሱፍ አል-ቀረዳዊ የሰጡትን ምላሽ እንደሚከተለው እናቀርባለን። እንዲህ ብለዋል፡-

“እኔ የሁለተኞቹን ሃሳብ እደግፋለሁ። ከርሱ ውጪ ያሉት አቋሞች በሙሉ ውድቅ ናቸው። የወረቀት ገንዘብ እንደ ወርቅና እንደ ብር ይታያል። ሰዎች ይገበያዩበት የነበረው የወርቅና የብር ገንዘብ እና አሁን ያለው -ሰዎች የሚገበያዩበት የወረቀት ገንዘብ- ተመሳሳይ ብይን አላቸው። በአሁኑ ዘመን ሰዎች ወርቅና ብርን ለመገበያያነት መጠቀም አቁመዋል። ወርቅና ብርን እንደመገበያያ መጠቀም ትተዋል። በዐለም ላይ የወረቀት ገንዘብ ብቸኛው የመገበያያ ገንዘብ ሆኗል። ሰዎች በወርቅና በብር መገበያየት ትተው በወረቀት ብር መገበያየት ጀምረዋል በሚል ሙግት የሪባን ብይን እንዴት እንተዋለን?

የወረቀት ገንዘቦች ባለቤት የሆነ ሰው ሰዎች ዘንድ ሀብታም ነው ተብሎ ይታሰባል። ኃብታሞች ላይ ግዴታ የሚሆነው ዘካም በርሱ ላይ ግዴታ ይሆናል። የወረቀት ገንዘቦች በብዛት ያለው ሰው ወርቅና ብር ስለሌለው ድሃ ነው ተብሎ ዘካ አይሰጠውም። የካበተ የወረቀት ገንዘብ ያለውን ሰው ድሃ ነው ያለ ሰው እንደ እብድ እና እንደ ቂል ይታያል። ሰዎች ሚስት ሲያገቡ እንደመህር ይከፍሉታል። ለድሃ ስትሰጠው በደስታ ይፈነጥዛል። ምክንያቱም የወረቀት ገንዘብ ገንዘብ ነው። ኃብት ነው። ሰዎች እቃ ይገዙበታል። የገዙትም የነርሱ ንብረት ይሆናል። ሰውየው ለተጠቀመው አገልግሎት ይከፍለዋል። አገልግሎት ሰጪውም እንደ ደም-ወዝ ይቀበለዋል። ሰው የገደለ ሰው የህይወት ካሳ አድርጎ ይከፍለዋል። ፀብንም ያበርዳል። ሌሎችም ወርቅና ብር የሚሰሯቸውን ሥራዎች በሙሉ ይሰራል። ሁሉም ዓይነት የቢዝነስ እንቅስቃሴዎች በዚሁ ገንዘብ ይከናወናሉ። ስለዚህ ሙሉ ለሙሉ የወረቀት ገንዘቦች የወርቅና የብር ገንዘቦችን ተክተው ይሰራሉ። ማንም ሰው ይህንን ሊጠራጠር አይገባም።

ጥርጣሬ ያለው ሰው ካለ ግን እነዚህን ወረቀቶች የነፍስ ካሳ አድርጎ እንዳይቀበል። ለሴት ልጁ ወይም ለእህቱ መህር አድርጎ እንዳይደራደር። ለሸቀጥም ዋጋ አድርጎ እንዳይከፍል፤ እንዳይገዛበት። የቤት ኪራይ አድርጎም እንዳይከፍለው። ሌሎችም የቢዝነስ እንቅስቃሴዎችን በሙሉ በነዚህ ወረቀቶች እንዳይከውን።

የወረቀት ገንዘቦች በሰዎች ቅቡል ስለሆኑና በባለስልጣኑ እውቅና ስለተሰጣቸው የዋጋ መተመኛ እና የመገበያያ ገንዘብ ሆነዋል። ስለዚህ የወርቅና የብር አይነት ኃይልን ተጎናፅፈዋል። ይህንን እውነታ ጥያቄ ውስጥ ለማስገባት የሚደረግ ማንኛውም ጥርጥርና ማምታቻ ተቀባይነት የለውም ብዬ አምናለሁ።

በወረቀት ገንዘብ አራጣን የበላ፣ ያስበላ እና በውሉ ሂደት ላይ የተሳተፈ ሰው ያለ ጥርጥር የሪባ/የወለድ/የአራጣው ኃጢያት ተካፋይ ነው። አላህና መልእክተኛውን ለመዋጋትም የቆረጠ ሰው ነው። በዚህ አይነት ውል ውስጥ ተሳታፊ የሆነ ሰው ሁሉ ተጠያቂ ነው። በሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ምላስ የተረገመ እርኩስም ነው። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) “ወለድ የሚበላን፣ የሚያስበላን፣ ፀሀፊውን እና ምስክሮቹን በሙሉ ረግመዋል።”

አላህ የበለጠ ያውቃል!