በኢሕራም ውስጥ የተከለከሉ ነገሮችን መፈፀምና ቅጣቱ

Home የፈትዋ ገጽ ሐጅና ዑምራ በኢሕራም ውስጥ የተከለከሉ ነገሮችን መፈፀምና ቅጣቱ

ጥያቄ፡ በኢሕራም ወቅት ክልክል የሆኑ ነገሮችን መፈፀም ብይኑ ምንድን ነው? ጥፋቱን የፈፀመ ሰውስ ምን ማድረግ ይጠበቅበታል?


መልስ፡- በኢሕራም ወቅት እርም የሆኑ ነገሮችን የፈፀመ ሰው የሚቀጣው ቅጣት እንደፈፀመው ነገር ይለያያል። ዐረፋ ላይ ከመቆሙ በፊት ወሲብ ፈፅሞ ከሆነ ሐጁ ይበላሽበታል። በሚመጣው ዓመት ቀዷ ከማውጣት ጋር ግመል ማረድ ግዴታ ይሆንበታል። አብዝሃኞቹ ዑለሞች ዘንድ ዐረፋ ላይ ከቆመ በኋላ ቢሆንም ቅጣቱ ተመሳሳይ ነው። ነገርግን ሐነፊዮች ይህኛው እርድ ዋጂብ ይሆንበታል እንጂ ዐረፋ ላይ እስከቆመ ድረስ ሐጁን አያበላሽበትም።

ሰውየው ያጠፋው ጥፋት አደን ማደን ከሆነ አምሳያውን- በዓይነት ወይም በዋጋ- መክፈል ግዴታ ይሆንበታል።

ሌሎች ጥፋቶችን ከሆነ የፈፀመው ፍየል ማረድ፣ ሦስት ቀን መጾም ዌይም ስድስት ሚስኪኖችን ማብላት ብቻ ነው የሚጠበቅበት።

የአውሮፓ የፈትዋና የምርምር ካውንስል ምክትል ፕሬዝዳንት የነበሩት ፈይሰል መውለዊይ- ረሂመሁላህ- እንዲህ ይላሉ፡-

በኢሕራም ወቅት እርም የሚሆኑ ነገሮችን የፈፀመ ሰው የሚቀጣው ቅጣት እን ጥፋቱ ዓይነት የተለያየ ነው። እንደሚከተለው ጠቅሰነዋል፡-

ወሲብ መፈፀም

ዐረፋ ላይ ከመቆሙ በፊት ወሲብ የፈፀመ ከሆነ ሐጁ እንደሚበላሽበት የዑለሞች ስምምነት (ኢጅማዕ) አለ። ሰውየው የቀሩትን የሐጅ ስራዎች የመከወን ግዴታ አለበት። ነገርግን ግመል ማረድ ግዴታው ነው። ከዚያም በመጪው ዓመት ቀዷእ ያወጣል። ይህ ቀዷ ሐጁ ግዴታ የሆነ ሐጁን ያፈረሰ ሰው ላይም ሆነ ግዴታ ያልሆነ ሐጅን ባበላሸ ሰው አይለይም። ሐነፊዮች ዘንድ ግን ፍየል ማረድ ግዴታ ይሆንበታል፤ ያፈረሰው ሐጁ ግዴታ ያልነበረ ከሆነ ቀዷ ግዴታ አይሆንበትም።

ወሲቡን የፈፀመው ዐረፋ ላይ ከቆመ በኋላ ከመጀመሪያው መፈታት በፊት (የዙልሒጃ አስረኛውን ቀን ላይ ጠጠር ሳይወረውር፣ ፀጉሩን ሳይላጭ ወይም በአላህ ቤት ላይ ጠዋፍ ሳያደርግ በፊት- ከእነዚህ ሦስቶቹ ሁለቱን ሳይሰራ-) ቢሆንም አብዝሃኞቹ ዑለሞች ዘንድ ተመሳሳይ ብይን ይሰጠዋል። ሐነፊዮች ዘንድ ግን በዚህ ሁኔታ ላይ ያለው ሰው ሐጅ አይበላሽም፤ ነገርግን ግመል ማረድ ግዴታ ይሆንበታል።

ወሲቡን የፈፀመው ከመጀመሪያው መፈታት በኋላ (ካለፉት ሦስት የአስረኛው ቀን ስራዎች ሁለቱን ከሰራ በኋላ) ከሆነ ሐጁን አያበላሽም። አብዝሃኞቹ ዑለሞች ዘንድ ቀዷእም የለበትም። ሻፊዒይ ዘንድ- ይህ ሰው- ግመል የማረድ ፊድያ (መቀጫ) ግዴታ ይሆንበታል። ኢማም ማሊክ ዘንድ ደግሞ ፍየል ማረድ ግዴታ ይሆንበታል።

አደን

يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا لَا تَقْتُلُوا الصَّيْدَ وَأَنتُمْ حُرُمٌ وَمَن قَتَلَهُ مِنكُم مُّتَعَمِّدًا فَجَزَاءٌ مِّثْلُ مَا قَتَلَ مِنَ النَّعَمِ يَحْكُمُ بِهِ ذَوَا عَدْلٍ مِّنكُمْ هَدْيًا بَالِغَ الْكَعْبَةِ أَوْ كَفَّارَةٌ طَعَامُ مَسَاكِينَ أَوْ عَدْلُ ذَٰلِكَ صِيَامًا لِّيَذُوقَ وَبَالَ أَمْرِهِ عَفَا اللَّهُ عَمَّا سَلَفَ وَمَنْ عَادَ فَيَنتَقِمُ اللَّهُ مِنْهُ وَاللَّهُ عَزِيزٌ ذُو انتِقَامٍ

“እናንተ ያመናችሁ ሆይ! እናንት በሐጅ ሥራ ውስጥ ስትኾኑ አውሬን አትግደሉ። ከእናንተም እያወቀ የገደለው ሰው ቅጣቱ ከእናንተ ሁለት የትክክለኛነት ባለቤቶች የሚፈርዱበት የኾነ ወደ ካዕባ ደራሽ መሥዋዕት ሲኾን ከቤት እንስሳዎች የገደለውን ነገር ብጤ መስጠት ወይም ምስኪኖችን ማብላት ወይም የዚህን ልክ መጾም ማካካሻ ነው። (ይኽም) የሥራውን ከባድ ቅጣት እንዲቀምስ ነው። (ሳይከለከል በፊት) ካለፈው ነገር አላህ ይቅርታ አደረገ። (ወደ ጥፋቱም) የተመለሰም ሰው አላህ ከርሱ ይበቀላል። አላህም አሸናፊ የመበቀል ባለቤት ነው።” (አል-ማኢዳ 5፤ 95)

አምሳያውን መክፈል ሲባል በቅርፁ አምሳያ የሆነ የቤት እንስሳ መክፈል ማለት ነው። አቡ ሐኒፋ ዘንድ ግን ተመጣጣኝ ዋጋውን መክፈል ማለት ነው። ሰውየው አምሳያውን መክፈል በማይችል ጊዜ ዋጋውን ይገምትና በዋጋው እህል ገዝቶ ሚስኪኖችን ያበላል። ይህንንም ካልቻለ በእያንዳንዱ እፍኝ (509 ግራም) አንድ ቀን ይጾማል።

የተጠቀሰው አንቀፅ አውቆ አውሬን በገደለ ሰው ላይ ይህንን ብይን ገልጧል። የሐጅ ስርዐት ውስጥ ከገባ (ኢሕራም ካደረገ) በኋላ አውሬ ያደነን ሰው እንደሚመለከትም በሐዲስ ዘገባዎች ተገኝቷል። ነገርግን ኃጢያተኛ አይሆንም። ይህ- ኢብኑ ከሲር እንደጠቀሱት- የአብዝሃኞቹ ዑለሞች ሃሳብ ነው።

የቀሩት ክልክል ነገሮች

ፀጉርን ያለ ጊዜው መላጨት፣ የተሰፋ ልብስ መልበስ እና መሰል የተከለከሉ ነገሮችን በመፈፀም ደግሞ አንድ ፍየል/በግ ማረድ ግዴታ ይሆናል። ወይም ሦስት ቀን መጾም ወይም ስድስት ሚስኪኖችን ሦስት ቁና እህል (9 ኪሎ ግራም) ማብላት ግዴታ ይሆናል። ይህ በከዕብ ቢን ዑጅራ የተዘገበውና ቡኻሪይ ያሰፈሩት ሐዲስ የሚያስረዳው ጉዳይ ነው። ኢማም ቡኻሪይ እዳስተላለፉት ባለማወቅ እና ረስቶ እነዚህን ክልክሎች መፈፀም ምንም ዓይነት ቅጣት አያመጣም።

ወላሁ አዕለም!