በቀን ሚስትን መሳም ፆምን ያበላሻል?

Home የፈትዋ ገጽ ዒባዳ ጾምና ኢዕቲካፍ በቀን ሚስትን መሳም ፆምን ያበላሻል?

ጥያቄ፡- ባል ሚስቱን መሳሙ ፆሙን ያበላሽበታል?


መልስ፡- ቡኻሪ እና ሙስሊም እንዲሁም አስሐቡ ሱነን የተሰኙት የሀዲስ ዘጋቢዎች ዓኢሻ (ረ.ዓ) እንዲህ ማለታቸውን ዘግበዋል፡-

كان رسول الله ـ صلى الله عليه وسلم ـ يُقَبل بعض أزواجه وهو صائم وكان أملكَكم لإِرْبِه

“የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ፆመኛ ሁነው ሚስቶቻቸውን ይስሙ ነበር። ታዲያ እርሳቸው ከማናችሁም በላይ ስሜታቸውን ይቆጣጠሩ ነበር።” (ቡኻሪና ሙስሊም)

በበይሀቂይ ዘገባ ከአዒሻ (ረ.ዓ) እንደተዘገበው መልእክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) ፆመኛ ሁነው ይስሟት ነበር። ምላሷንም ይመጡት ነበር።

ማሊክ ሙወጧእ የተሰኘው መፅሀፋቸው ላይ ዓኢሻ ቢንት ጦልሐ ቢን ዑበይዲላህ የተባለችዋን የአዒሻ (ረ.ዓ) ወንድም የዓብዱርራህማን ቢን አቢበክር (ረ.ዐ) ሚስት ዋቢ በማድረግ እንደዘገቡት ሴቲቱ እናታችን አዒሻ ጋር እያለች ባሏ -ዓብዱርራህማን- ወደቤት ገባ። ከዚያም እናታችን አዒሻ (ረ.ዓ) እንዲህ አለችው፡- “ለምንድን ነው ወደ ሚስትህ የማትቀርበው? የማትስማትና የማታጫውታት?” እርሱም እንዲህ አለ፡- “ፆመኛ ሁኜ ልሳማት?” አዒሻም እንዲህ አሉ፡- “አዎን!”

ከዑመር ኢብኑል ኸጧብ (ረ.ዐ) እንደተዘገበው እርሳቸው እንዲህ ብለዋል፡- “አንድ ጊዜ ሚስቴን በረመዷን በቀን ሳምኳት እና ወደ መልእክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) በመምጣት ያረሱለላህ ዛሬ ቀን ከባድ ወንጀል ፈፅሜያለሁ፣ ፆመኛ ሆኜ ሚስቴን ሳምኩኝ አልኳቸው። እርሳቸውም እንዲህ አሉ፡- “ፆመኛ ሆነህ በውሀ ብትጎማመጥ ፆምህን ያጠፋል?” እኔም አዬ ችግር የለውም አልኩኝ። “ታዲያ ዝም በላ!” (በሌላ ዘገባ “ታዲያ ምንድን ነው የምትጠይቀው?!”) አሉኝ።” (አቡዳዉድ እና ነሳኢይ ዘግበውታል)።

በነዚህ ዘገባዎች በመመራት ኢብኑል ሙንዚር እንዲህ ብለዋል፡- ዑመር፣ ኢብኑ ዓባስ፣ አቡ ሁረይራ እና ዓኢሻ ፆመኛ ሚስቱን መሳም እንደሚፈቀድለት ገልፀዋል። አህመድ እና ኢስሀቅም ይህንኑ መንገድ ይዘዋል። ሀነፊዮችና ሻፊዒዮች ግን ስሜቱን መቆጣጠር የሚከብደው ከሆነ ይጠላበታል፤ ስሜቱን የማያንቀሳቅስበት ከሆነ ደግሞ አይጠላበትም፤ ነገርግን መተዉ ይሻለዋል ብለዋል።

ማሊኪዮች ደግሞ- አልዙርቃኒይ አልመዋሂብ የተሰኘው መፅሀፋቸው ቅፅ 5፤ ገፅ 227 ላይ እንደጠቀሱት- ፍትወት ይወጣኛል ብሎ ከፈራ ሐራም ነው፤ ይህን ካልፈራ ግን ይጠላል ብለዋል።

ኢማም ኢብኑ ሀጀር እንዲህ ብለዋል፡- ሀራም ወደሚሆነው ግንኙነት (ወሲብ) ወይም መንይን (ፍትወትን) ወደማፍሰስ የማያደርሰውና እራሱን የሚቆጣጠር ከሆነ ይፈቀዳል።

ሌሎች ደግሞ (ዟሂሪዮች ይባላሉ) በፆም ውስጥ ሚስትን መሳም ወደ አላህ መቃረቢያ ነው አሉ። ወደዚያ የመራቸው ከሀዲሶቹ የላይ ትርጉም የወሰዱት ግልብ ግንዛቤ ነው። ይህ ሀሳብ ውድቅ ነው። ምክንያቱም ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ስሜታቸውን ይቆጣጠራሉ፤ ስለዚህ እርሳቸው በዚህ ጉዳይ ላይ እንደሌላው ሰው አይደሉም። ስለዚህ ሌሎች ሰዎች በርሳቸው አይመሰሉም።

አላህ የተሻለ ያውቃል!