በቀብር ወቅት ዱዐ ማድረግ

Home የፈትዋ ገጽ ጀናኢዝ በቀብር ወቅት ዱዐ ማድረግ

ጥያቄ:-  የሞተን ሰው የሚሸኙ ሰዎች ምን ያድርጉ? ድምፃችንን ከፍ አድርገን በህብረት ለሞተ ሰው ዱዐ ማድረግ እንችላለን? 


መልስ:- ለተመሳሳይ ጥያቄ የግብፁ ዳሩል-ኢፍታእ የሚከተለውን መልስ አስፍሯል፡-

ከቀብር ስነስርዐት በኋላ ሸኚዎቹ በቀብሩ ላይ ቆይተው ለሟቹ ዱዐ ማድረግ ይወደድላቸዋል። ምክንያቱም አቡዳዉድና ሐኪም- በሶሒሕ ሰነድ- ከዑስማን ይዘው እንደዘገቡት የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) የሞተን ሰው ቀብረው ካገባደዱ በኋላ ቀብሩ ላይ በመቆም እንዲህ ይሉ ነበር:-

 استغفروا لأخيكم وسلوا له التثبيت فإنه الآن يسأل

“ለወንድማችሁ ምህረት ለምኑ። አላህ (በመላኢካዎቹ ምርመራ ላይ) ፅናት እንዲሰጠው ለምኑለት። እርሱ አሁን ይጠየቃል።”

ዐምር ቢን አል-ዐስ እንዲህ ማለታቸው ተዘግቧል:-

إذا دفنتموني فشنوا علي التراب شنا. ثم أقيموا حول قبري قدر ما تنحر الجزور ويقسم لحمها حتى أستأنس بكم وأنظر ماذا أراجع رسل ربي

“ስትቀብሩኝ አፈርን በእኔ ላይ እርጩ። ከዚያም  በእናንተ እንድፅናና እና ለጌታዬ መልእክተኞች ምን እንደምመልስ እንዳስብ ግመል ታርዶ ስጋው በሚከፋፈልበት ልክ እኔ ዘንድ ቆዩልኝ።” ሙስሊም ዘግበውታል።

ይህ ቆይታ ከቀብር በኋላ የሚደረግ ቆይታ ነው።

ከዱዐው በፊት ሞትን የሚያስታውስ አጭር ምክር ወይም ተግሳፅ ቢኖር ችግር የለውም። ምክንያቱም ቀልብን ያቀጥናል። ለአላህ ለመዋረድና ለመተናነስ፣ ስሜትንም ለመሰብሰብ ይጠቅማል።

ዐሊይ እንዲህ ይላሉ:- በቂዕ የሚባለው የመቃብር ቦታ ላይ አንድን አስክሬን እየቀበርን ነበር። ከዚያም የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ወደኛ መጡና ተቀመጡ። እኛም ዙርያቸው ተቀመጥን። አንዲት አንካሴ ይዘው ነበር። አቀረቀሩና በአንካሴያቸው መሬቱ ላይ አሰመሩ። ከዚያም እንዲህ አሉ:-

ما منكم من أحد وما من نفس منفوسة إلا كتب مقعدها من الجنة والنار. وإلا قد كتب شقية وسعيدة

“ማናችሁም- የተፈጠረች ነፍስ ሁላ- የጀነትም ሆነ የጀሀነም ቦታዋ ተፅፎላታል። እድለኛም ሆነ መናጢነቷም ተከትቦባታል።” 

ከዚያም አንድ ሰው ተነሳና “የአላህ መልእክተኛ ሆይ በመዝገባችን እንደገፍ?” አላቸው።

እርሳቸውም:-

اعملوا فكل ميسر لما خلق له

“ሥሩ። ሁሉም ለተፈጠረለት ነገር የተገራ ነው! አሉ።” ቡኻሪይና ሙስሊም ዘግበውታል።

ቡኻሪይ “ሶሒሕ” በሚሰኘው መፅሐፋቸው ላይ ለዚህ ጉዳይ አንድ ሙሉ ምዕራፍ ትተዋል። “ باب مَوعِظةِ المُحَدِّثِ عندَ القَبرِ وقُعُودِ أَصحابِه حَولَهአንድ ሰው ቀብር ላይ ምክር ሊሰጥና ባልደረቦቹም በዙርያው ሊቀመጡ እንደሚችሉ የሚናገር ምዕራፍ” ብለውም ሰይመውታል።

ኢማም አን-ነወዊይ አል-አዝካር የተሰኘው መፅሀፋቸው ገፅ 161 ላይ እንዲህ ይላሉ:-

“ቀብረው ከጨረሱ በኋላ ግመል ታርዶ ስጋው መከፋፈል ለሚችልበት ጊዜ ያህል ቢቀመጡ መልካም ነው። ቀብሩ ላይ የሚቆዩ ሰዎችም ቁርኣን በማንበብ፣ ለሟቹ ዱዐ በማድረግ፣ ተግሳፅ በመስማት፣ የደግ ሰዎችን ታሪክና ጠባይ በማውራት ቢጠመዱ መልካም ነው። ሻፊዒይና ታላላቅ ተማሪዎቻቸው እንዲህ ይላሉ:- ‘ቀብሩ ዘንድ ቁርኣን ቢያነቡ መልካም ነው።’ እንደውም ‘ከመጀመሪያ እስከመጨረሻው ቢያኸትሙ ጥሩ ነው።’ ይላሉ።”

ለሞተ ሰው ዱዐ የሚደረግበት ሁኔታን አስመልክቶ የተለየ ዘገባ የለም። በድብቅ ይሁን ድምፅ ከፍ ተደርጎ?… በግል ይሁን በህብረት?… የተለየ ዘገባ የለም። ስለዚህ ጉደዩ ሰፊ ነው ማለት ነው። በዚህ ዙርያ መጨቃጨቅ አላህ የማይወደው ስራ ነው። እንደውም በዚህ ምክንያት መጨቃጨቅ የተወገዘ “ቢድዐ” ነው። ምክንያቱም አላህ ያሰፋውን ማጣበብ ቢድዐ ነው። አፈፃፀሙ ሊገለፅባቸው የሚችልባቸው የተለያዩ አኳኋኖች እያሉ አንድን ነገር- አላህ- ስድ (ሙጥለቅ) አድርጎ ሲደነግግ በስድነቱ ነው የሚያዘው። ስፋቱ እንደተጠበቀ ነው የሚከወነው። አንዱን አፈፃፀም ከሌላው መለየት አይቻልም።

የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ጥያቄ ማብዛት ከልክለዋል። አላህ አንድን ነገር ዝም ሲል ጉዳዩን ማስፋት እና ለኡመቱ ማዘን መፈለጉን፣ ረስቶት አለመሆኑን በይነዋል። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ይላሉ:-

إن الله فرض فرائض فلا تضيعوها، وحرم حرمات فلا تنتهكوها، وحد حدودا فلا تعتدوها، وسكت عن أشياء رحمة لكم غير نسيان فلا تبحثوا عنها

“አላህ ግዴታዎችን ደንግጓል፤ አታጓድሏቸው። እርም ነገሮችን ደንግጓል። አትተላለፏቸው። አንዳንድ ድንበሮችን ወስኗል፤ አትጣሷቸው። አንዳንድ ነገሮችን ዝም ብሏል- ለእናንተ አዝኖ እንጂ ረስቶ አይደለም። ስለዚህ አትመራመሩባቸው።” ዳረቁጥኒይና ሌሎችም ከአቡ ሰዕለባ አል-ኹሸኒይ ዘግበውታል። ነወዊይም ሐዲሱን “ሐሰን” ነው ብለዋል። ታላቁ ዐሊም ሰዕድ አት-ተፍታዛኒይ “ሸርሑል-አርበዒን አን-ነወዊያ” ገፅ 191 ላይ እንዲህ ይላሉ:- “አትመራመሩባቸው” ማለት አትጠይቁ ማለት ነው። ምክንያቱም አላህ ዝም ያለበትን ነገር መጠየቅ ከባባድ ወደሆኑ ድንጋጌዎች ይወስዳል። ስለዚህ በእንዲህ አይነት ጉዳዮች ላይ ‘በመሰረታዊው የሰዎች ጫንቃ ንፅህና’ (በራኣቱል-አስሊያ) ይፈረዳል።”

በመመራመሩና አጥብቆ በመጠየቁ ምክንያት ሙስሊሞች ላይ ጥበት የፈጠረ ሰውን የአላህ መልእክተኛ አውግዘዋል። ከዓሚር ቢን ሰዕድ ከአባታቸው እንደተዘገበው የአላህ ነብይ እንዲህ ይላሉ:-

أَعظَمُ المُسلِمِينَ في المُسلِمِينَ جُرمًا رَجُلٌ سأَلَ عن شَيءٍ ونَقَّرَ عنه فحُرِّمَ على النّاسِ مِن أَجلِ مَسأَلَتِه

“ከሙስሊሞች መሀል ከባድ ወንጀለኛ ማለት አንድን ነገር የጎረጎረና አጥብቆ የጠየቀ፣ በርሱም ሰበብ ሰዎች ላይ እርም ያስደረገ ሰው ነው።” ሙስሊም ዘግበውታል።

አቡሁረይራ እንደዘገቡት የአላህ ነብይ:- “ሰዎች ሆይ አላህ በናንተ ላይ ሐጅን ግዴታ አድርጓል። ሐጅ አድርጉ።” አሉ። ከዚያም አንድ ሰው ተነሳና “በየዐመቱ ነው? የአላህ መልእክተኛ!” አለ፤ ሦስት ጊዜ የአላህ መልእክተኛ ዝም ቢሉትም። ከዚያም እንዲህ አሉ:- “የተውኳችሁን ተዉኝ። ከናንተ በፊት የነበሩ ሰዎች የጠፉት ጥያቄ በማብዛታቸውና በነብያቶቻቸው ላይ ወሰን በማለፋቸው ነው። አንድን ነገር ሳዛችሁ ከርሱ የቻላችሁትን ስሩ። ስከለክላችሁም ተዉት።” ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል።

ታላቁ ዐሊም አል-ሙናዊ “ፈይዱል-ቀዲር ሸርሑል-ጃሚዒስ-ሰጊር” ገፅ 3562 ላይ እንዲህ ብለዋል:- “ይህ ማለት (ያለፈውን ሐዲስ እያብራሩ ነው) እናንተን እስከተውኳችሁ ድረስ እናንተም እኔን መጠየቅ ተዉ። እኔ እስካልነገርኳችሁ ድረስ የማይጠቅማችሁን የዲን ጥያቄ እኔን ለመጠየቅ አታስቡ። ምናልባት ይህ ስራችሁ ጥብቅ የሆነ ትዕዛዝ ሊያመጣ ይችላልና። ያዘዝኳችሁን ነገር ይፋዊ ትርጉም ያዙ። የመፅሀፍቱ ባለቤቶች እንዳደረጉት አትመራመሩ። በግልፅ የተነገራችሁ ነገር ሌሎች ሁኔታዎች ቢኖሩትንኳ እስከጥጉ አትጠይቁኝ። ምክንያቱም የምሰጣችሁ መልስ ሊበዛና ሊጠብቅባችሁ ይችላል። በዚህ ምክንያትም የእስራኤል ልጆች ላይ እንደተከሰተው አይነት እናንተም ላይ ሊከሰት ይችላል። እነርሱ አጠበቁና አላህም አጠበቀባቸው። የአላህ መልእክተኛም ይህ ችግር ህዝባቸው ላይ እንዲከሰት ስላልፈለጉ ማስጠንቀቃቸው ነው።”

ይህ እንዲሁ እንዳለም የጀመዐ ዱዐ ለቀቡልነት ቅርብ ነው። ልብንም ያነቃቃል። ስሜትን ይሰበስባል። ለመተናነስና- ለአላህ- ለመዋረድ ይጋብዛል።

ከኢብኑ ዐባስ እንደተዘገበው የአላህ መልእክተኛ እንዲህ ብለዋል:- “አላህ እርዳታ ያለው ከህብረት ጋር ነው።” ቲርሙዚይና ነሳኢይ ዘግበውታል። ቱርሙዚይ “ሐሰን” ነው ብለዋል።

ወላሁ አዕለም!