በሶላት ውስጥም ሆነ ከሶላት ውጪ ከዱዐ በኋላ ፊትን በእጆች መዳበስ

Home የፈትዋ ገጽ ዚክርና ዱዓ በሶላት ውስጥም ሆነ ከሶላት ውጪ ከዱዐ በኋላ ፊትን በእጆች መዳበስ

ጥያቄ፡- ከዱዐ በኋላ ፊትን በእጆች መዳበስ እንዴት ይታያል?


መልስ፡- ዱአዕ ወደ አላህ ከሚያቃርቡ ታላላቅ ስራዎች መካከል አንዱ ነው። አላህን እጅግ መፈለግና እርሱን መከጀል የሚታይበት ተግባር ነው። ሰውየው የራሱን ድህነትና የአላህን ሀብታምነት የሚያውጅበትም ድርጊት ነው። የአላህ ነብይ (ሰ.ዐ.ወ) አምልኮ (ዒባዳ) ብለው ሰይመውታል። አቡ ዳዉድ፣ ቲርሙዚይ (ሶሒሕ አድርገውት)፣ አሕመድ፣ ኢብኑ ሒባን፣ አል-ሐኪም (ሶሒሕ አድርገውት) ከኑዕማን ቢን በሺር እንደዘገቡት የአላህ ነብይ (ሰ.ዐ.ወ)፡-

الدعاء هو العبادة

“ዱዓ አምልኮ ነው።” አሉ። ከዚያም ተከታዩን አንቀፅ አነበቡ።

وَقَالَ رَبُّكُمُ ادْعُونِي أَسْتَجِبْ لَكُمْ إِنَّ الَّذِينَ يَسْتَكْبِرُونَ عَنْ عِبَادَتِي سَيَدْخُلُونَ جَهَنَّمَ دَاخِرِينَ

“ጌታችሁም አለ ‘ለምኑኝ፤ እቀበላችኋለሁና፡፡ እነዚያ እኔን ከመግገዛት የሚኮሩት ተዋራጆች ኾነው ገሀነምን በእርግጥ ይገባሉ’፡፡” (ጋፊር፤ 60)

አላህ ዱዐ እንድናበዛ አዞናል። አብዝቶም ቀስቅሶናል። እንዲህ ይላል፡-

وَاسْأَلُوا اللَّهَ مِن فَضْلِهِ

“አላህንም ከችሮታው ለምኑት፡፡” (አን-ኒሳእ፤ 32)

በሌላ አንቀፅም እንዲህ ይላል፡-

فَادْعُوا اللَّهَ مُخْلِصِينَ لَهُ الدِّينَ وَلَوْ كَرِهَ الْكَافِرُونَ

“አላህንም ከሓዲዎች ቢጠሉም ሃይማኖትን ለእርሱ አጥሪዎች ኾናችሁ ተገዙት፡፡” (ጋፊር፤ 14)

በሌላ ስፍራም እንዲህ ይላል፡-

ادْعُوا رَبَّكُمْ تَضَرُّعًا وَخُفْيَةً إِنَّهُ لَا يُحِبُّ الْمُعْتَدِينَ  *  وَلَا تُفْسِدُوا فِي الْأَرْضِ بَعْدَ إِصْلَاحِهَا وَادْعُوهُ خَوْفًا وَطَمَعًا إِنَّ رَحْمَتَ اللَّهِ قَرِيبٌ مِّنَ الْمُحْسِنِينَ

“ጌታችሁን ተዋርዳችሁ በድብቅም ለምኑት፡፡ እርሱ ወሰን አላፊዎችን አይወድምና፡፡  በምድርም ውስጥ ከተበጀች በኋላ አታበላሹ፡፡ ፈርታችሁና ከጅላችሁም ተገዙት፡፡ የአላህ ችሮታ ከበጎ አድራጊዎች ቅርብ ነውና፡፡” (አል-አዕራፍ፤ 55-56)

የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ዱዐ መተው እንደሌለብን አሳስበዋል። አላህን መለመን ማቋረጥ እንደማይገባን አስጠንቅቀዋል። ቡኻሪይ “አደቡል-ሙፍረድ” ላይ፣ ቲርሙዚይ እና አል-ሐኪም -ሙስተድረክ ላይ- ሰነዱን ሶሒሕ አድርገውት አቡ ሁረይራን ዋቢ በማድረግ እንደዘገቡት የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ይላሉ፡-

من لم يسأل الله يغضب عليه

“አላህን የማይለምነው ይቆጣበታል።”

ሰውየው እጆቹን ወደ አላህ ከፍ እስካደረገ ድረስ አላህም በባዶ አይመልስበትም። ራሱን ለአላህ ልቅና አዋርዶ በከጃይነት መንፈስ እስከተለማመጠው ጉዳዩን መፈፀሙ አይቀርም። ሰውየው በጉዳዩ ላይ አላህን እስከለመነው ድረስ -ጉዳዩ ቢሳካማ ባይሳካም- ሃሳቡን እና ምኞቱን ይባርክለታል። አሕመድ እና ሐኪም -ሶሒሕ አድርገውት- አቡ ሰዒድ አል-ኹድሪይን ዋቢ በማድረግ እንደዘገቡት የአላህ ነብይ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ይላሉ፡-

ما من مسلم يدعو الله بدعوة ليس فيها إثم ولا قطيعة رحم إلا أعطاه الله بها إحدى ثلاث: إما أن يعجل له دعوته، وإما أن يدخرها له في الآخرة، وإما أن يصرف عنه من السوء مثلها

“ማንኛውም ሙስሊም ኃጢያትና ዝምድናን መቁረጥ ያልታከለበት ምንም ዓይነት ዱዐ ካደረገ አላህ ከሦስት ነገሮች አንዱን ሳይሰጠው አይቀርም። ዱዐውን በፍጥነት ይሞላለታል። ወይም ለአኺራው ያከማችለታል። ወይም የልመናውን የሚያህልን ክፉ መዐት ይጠብቀዋል።”

“ታላላቅ የፊቅህ ልሂቆች ዱዐን ካገባደዱ በኋላ ፊትን ማበስ ይወደዳል ብለው በግልፅ አስፍረዋል። ፊት የሚታበሰው አላህ ለዱዓ የተዘረጋን እጅ ባዶውን አይመልሰውም ከሚለው ሃብ ጋር በተያያዘ እጅ ላይ ራሕመት አርፏል ከሚል በጎ ጥርጣሬ የመነጨ እንደሆነ ይነገራል። ፊትን ከሌሎች አካላቶች ለይቶ ማበስ የተመረጠበት ምክንያት ፊት ክቡሩ አካል ስለሆነ ነው።” (ሱቡሉ-ስ-ሰላም፤ አስ-ሰንዓኒይ፤ ቅፅ 2፤ ገፅ 709)

“ሐሺየቱ-ሽ-ሸርነበላሊይ ዓላ ዱረሪል-ሑካም” የተሰኘው የሐነፊዮቹ መፅሐፍ ቅፅ 1፤ ገፅ 80 ላይ “የሶላት አሰጋገድ” የሚሰኘው ምዕራፍ ላይ ከሶላት በኋላ የሚደረጉ ዚክሮችና ዱዓዎችን ከጠቀሰ በኋላ እንዲህ ይላል፡- “ከዚያም ሰውየው (ዱዓዎቹን) ‘ሱብሐነ ረብ-ቢከ’ በማለት ያጠናቅቃቸው። ዐሊይ እንዲህ ይላሉ፡- ‘የቂያም ቀን ምሉዕ በሆነ ሚዛን ላይ መመዘን የሚሻ ሰው ከተቀመጠበት ሲነሳ የሚናገረው የመጨረሻው ንግግሩ ‘ሱብሐነ ረብ-ቢከ’ ይሁን።’

በተጨማሪም ፊቱን እና መዳፎቹን ይዳብስ። ምክንያቱም ዐብዱላህ ኢብኑ ዐባስ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል ይላሉ፡-

إذا دعوت الله فادع بباطن كفيك ولا تدع بظهورهما فإذا فرغت فامسح بهما وجهك

“አላህን ስትለምን በውስጥ መዳፍህ ለምነው። በእጆችህ ጀርባ አትለምን። ስትጨርስ ደግሞ ፊትህን በመዳፎችህ ዳብስ።” ኢብኑ ማጀህ ዘግበውታል።”

አል-ነፍራዊይ “አል-ፈዋኪሁድ-ደዋኒ” የተሰኘው የማሊኪያ መዝሀብ መፅሀፍ -ቅፅ 1፣ ገፅ 335- ላይ እንዲህ ይላሉ፡- “ከዱዐእ በኋላ ልክ የአላህ ነብይ ያደርጉት እንደነበረው ፊቱን እና እጆቹን መዳበስ ይወደዳል።”

ከሻፊዒዮቹ መካከልም -ኢማም ነወዊይ- አል-መጅሙዕ ላይ የዱዓ ስነስርዐቶችን ሲያብራሩ እንዲህ ይላሉ፡- “ዱዐውን በተከበሩት ወቅቶች፣ በተከበሩት ስፍራዎች፣ በተከበሩ ሁኔታዎች ላይ ማድረግ የዱዐው ስነስርዐት ነው። ወደ ቂብላ መዞር፣ ዱዐውን ሲጨርስ ፊቱን መዳበስ፣ ድምፅን ዝግ በማድረግ – በዝምታና በመጮህ መካከል ማድረግ ተወዳጅ ስነስርዐት ነው።” አል-መጅሙዕ፤ ቅፅ 4፤ ገፅ 487።

ሸይኹል-ኢስላም ዘከሪያ አል-አንሷሪይ አስነል-መጧሊብ የተሰኘው መፅሀፋቸውነ -ቅፅ 1፣ ገፅ 160- ላይ እንደገለፁት ነወዊይ ከዱዐእ በኋላ ፊትን በእጆች መዳበስ ሱና መሆኑን በእርግጠኝነት ተናግረዋል። አል-ኸጢብ አል-ሺርቢኒም “ሙግኒል-ሙሕታጅ” ቅፅ 1፣ ገፅ 370- ላይ ይህንኑ ገልፀዋል።

ታላቁ የሐንበሊያ መዝሀብ ዐሊም አል-ቡሁቲይም እንዲህ ይላሉ፡- “ከዚያም እዚህ ስፍራ ላይ (ከቁኑት በኋላ) ፊቱን ይዳብሳል። ከሶላት ውጪ ዱዐ ሲያደርግም እንዲሁ ያደርጋል።” ሸርሑ ሙንተሃል-ኢራዳት ቅፅ 1፣ ገፅ 241። አል-ኢንሷፍ የተሰኘውን ተመሳሳይ መፅሀፍ ቅፅ 2፣ ገፅ 173 ላይ እና ከሽ-ሻፉል-ቂናዕ ቅፅ 1፣ ገፅ 420 ላይ ተመልከት።

ማስረጃችን የነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ሐዲስ ነው። ቲርሙዚይና አል-ሐኪም ከዑመር እንደዘገቡት “የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ለዱዐ እጃቸውን ከዘረጉ በኋለላ ፊታቸውን ሳይዳብሱ አይመልሱትም ነበር።”

አል-ሐፊዝ ኢብኑ ሐጀር “ቡሉጉል-መራም” ላይ እንዲህ ይላሉ፡- “ይህንን ሐዲስ ቲርሙዚይ ዘግበውታል። ደጋፊ ዘገባዎችም አሉት። ከእነርሱም መሀል ከኢብኑ ዐባስ የተዘገበ – የአቡዳዉድ ሐዲስ አለ። የዘገባዎቹ ድምር ሐዲሱን የሐሰን ደረጃ ላይ ያስቀምጡታል።”

አል-ሰንዐኒይ “ሱቡሉስ-ሰላም” የተሰኘው መፅሀፍ ቅፅ 2፣ ገፅ 709 ላይ እንዲህ ይላሉ፡- “ይህ ሐዲስ ዱዐን ካገባደዱ በኋላ ፊትን ማበስ እንደሚወደድ ያስረዳል።”

ሌላም ማስረጃ አለ። አቡ ዳዉድ፣ ኢብኑ ማጀህ፣ ሐኪም እና በይሀቂይ ከኢብኑ ዐባስ እንደዘገቡት የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ይላሉ፡-

سلوا الله ببطون أكفكم ولا تسألوه بظهورها، فإذا فرغتم فامسحوا بها وجوهكم

“በውስጥ መዳፋችሁ አላህን ለምኑት። በጀርባው አዙራችሁ አትለምኑት። ስትጨርሱ ደግሞ ፊታችሁን ዳብሱ።”

ሲዩጢይ የሸይኹል-ኢስላም አቢል-ፈድል ቢን ሐጀርን “አማሊይ” የተሰኘ መፅሀፍን በመጥቀስ “ሐዲሱ ሐሰን ነው።” ብለዋል። ፈድ-ዱል-ዊዓእ የተሰኘውን የኢማም ሲዩጢይን መፅሀፍ ገፅ 74 ተመልከት።

“ሱነኑ አቢዳዉድ” እና “ሙስነዱ አሕመድ” ላይ ከየዚድ ቢን ሰዒድ ቢን ሱማማ እንደዘገቡት “የአላህ ነብይ (ሰ.ዐ.ወ) ዱዐ ሲያደርጉ እጆቻቸውን ከፍ ያደርጉ ነበር። ከዚያም ፊታቸውን ይዳብሱ ነበር።”

ሶሐቦቹ ለዱዐ እጆቻቸውን ከፍ ካደረጉ በኋላ ፊታቸውን በእጆቻቸው መዳበሳቸውን የሚጠቁሙ ዘገባዎችም አሉ። ከእነዚህ መሀል ኢማም አል-ቡኻሪይ “አደቡል-ሙፍረድ” የተሰኘው መፅሀፋቸው ላይ “በዱዐ ወቅት እጅን ስለማንሳት” በሚያብራራው ምዕራፍ ላይ የዐብዱላህ ቢን ዑመርንና ኢብኑ ዙበይርን በመጥቀስ ከዱዐ በኋላ ፊትን መዳበስ እንደሚወደድ ሲያብራሩ እንዲህ ይላሉ፡-

حدثنا إبراهيم بن المنذر قال: حدثنا محمد بن فليح قال: أخبرني أبى عن أبى نعيم وهو وهب قال: رأيت ابن عمر وابن الزبير يدعوان يديران بالراحتين على الوجه

“ኢብራሂም ቢን አል-ሙንዚር እንዳወሩት፣ ሙሐመድ ቢን ፉለይሕ እንደዘገቡት፣ አቡ ኑዐይም -ወህብ ነው ስማቸው- እንዲህ ሲሉ ነግረውናል፡- ኢብኑ ዑመርና ኢብኑ ዙበይር ዱዐ አድርገው ሲያገባድዱ እጆቻቸውን ፊታቸው ላይ ያሽከረክሩት ነበር።” ቡኻሪይ፤ አደቡል-ሙፍረድ፤ ቅጽ 1 ገፅ 214።

ኢማም ሲዩጢይ “ፈድ-ዱል-ዊዓእ” የተሰኘው መፅሃፋቸው ገፅ 101 ላይ ይህንን በድርጊት ሐሰን አል-በስሪይ ይፈፅሙት እንደነበር ዘግበዋል። “አል-ፊርያቢይ እንዲህ ይላሉ፡- ኢስሐቅ ቢን ራሃወይህ እንዳወሩት፣ ሙዕተሚር ቢን ሱለይማን እንደነገሩን እንዲህ ይላሉ፡- አቡ ከዕብን እጃቸውን ከፍ አድርገው ዱዐ ሲያደርጉ አይቻቸዋለሁ። ከዚያም ዱዐቸውን ሲያገባድዱ ፊታቸውን ዳበሱ። ‘ይህንን ስራ ማን ሲሰራው አይተህ ነው?’ ብዬ ጠየኩት። እርሳቸውም ‘አል-ሐሰን ቢን አቢል-ሐሰንን አይቼ ነው።’ አሉ።”

የቁኑት ዱዐ ካለቀ በኋላ ፊትን በእጆች መዳበስ ሱና መሆኑ ከሻፊዒዮች ቃዲ አቡ ጦይብ፣ ሸይኽ አቡ ሙሐመድ አል-ጁወይኒይ፣ ኢብኑ ሶባግ፣ ሙተወሊ፣ ገዛሊ እና አል-ዑምራኒይ የሄዱበት አንዱ መንገድ ነው። አል-መጅሙዕ የተሰኘውን የነወዊን መፅሀፍ ቅፅ 3፣ ገፅ 500-501 ተመልከት።

በኢማም አሕመድ መዝሀብም ይህ አቋም ቀቡል ያለው የተሻለው መንገድ ነው። ከላይ ከታላቁ ዐሊም አል-ቡሁቲይ የጠቀስነውን ተመልከት።

በዚህ መሰረት ከዱዐ በኋላ ፊትን በእጆች መዳበስ ይፈቀዳል። ምንም ዓይነት ችግርም የለበትም። እንደውም ከዱዐ ስነስርዐቶች መሀል የሚጠቀስ ነው። ተወዳጅ ድርጊት ነው። ዑለሞች በመፅሀፍቶቻቸው ላይ ጠቅሰውታል። በየከተማውና በየዘመኑ የተከሰቱ ሙስሊሞችም ሰርተውበታል።

ወላሁ አዕለም!