በረመዳን ጥርስን ማፅዳት “የጾመኛ የአፍ ጠረን አላህ ዘንድ ከሚስክ ሽታ በላይ ተወዳጅ ነው።” ከሚለው ነብያዊ ሐዲስ ጋር ይጋጫል?

Home የፈትዋ ገጽ ጾምና ኢዕቲካፍ በረመዳን ጥርስን ማፅዳት “የጾመኛ የአፍ ጠረን አላህ ዘንድ ከሚስክ ሽታ በላይ ተወዳጅ ነው።” ከሚለው ነብያዊ ሐዲስ ጋር ይጋጫል?

ጥያቄ፡- ጥርስን ማፅዳት በሸሪዐው በጥብቅ የታዘዘ መሆኑ ይታወቃል። ነገርግን ይህ ሸሪዐዊ ትዕዛዝ የጾመኛን የአፍ ጠረን ከሚያሞግሰው ሐዲስ ጋር አይጋጭም?


መልስ፡- ቢስሚላሂር-ረሕማኒር-ረሒም። አልሐምዱሊላሂ ረቢል-ዐለሚን። ወስ-ሶላት ወስ-ሰላም ዓላ ረሱሊላህ ወበዕድ፡-

ቡኻሪይ እና ሙስሊም ከነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ የሚል ንግግር ዘግበዋል፡-

والذي نفس محمد بيده لخلوف فم الصائم أطيبُ عند الله من ريح المسك

“የሙሐመድ ነፍስ በእጁ በሆነው ጌታ እምላለሁ የጾመኛ የአፍ ጠረን አላህ ዘንድ ከሚስክ ሽታ የበለጠ ተወዳጅ ነው።”

በሌላ በኩልም አቡዳዉድ እና ቱርሙዚይም ከዓሚር ኢብኑ ረቢዐህ እንዲህ የሚል ዘግበዋል፡-

رأيتُ رسول الله ـ صلى الله عليه وسلم ـ يتسوّك ما لا أُحصي وهو صائم

“የአላህን መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) በቁጥር ልጠቅሰው የማይቻለኝን ያህል ጊዜ ጾመኛ ሆነው ጥርሳቸውን ሲፍቁ አይቻቸዋለሁ።”

ኢማም ሻፊዒይ ከመጀመሪያው ሐዲስ በመነሳት ጥርስን በመፋቂያ -ወይም በቡሩሽ- መፋቅ የተጠላ መሆኑን አመልክተዋል። መጠላቱንም ከዙህር ሶላት ወቅት በኋላ ባለው ጊዜ ገድበውታል። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ያሞገሱት የተበላሸውን የጾመኛን የአፍ ጠረን እንዳይወገድ ለማድረግ ነው ይጠላል ያሉት። የአፍ ጠረን መለወጥ ምግብና መጠጥ ካለመቅመስ የሚመጣ ነው። በተለይም ይህ የሚከሰተው ፀሀይ ወደ ምዕራብ ከምትዘነበልበት -የዙህር ሶላት ወቅት- ጀምሮ ነው።

ኢማም ሻፊዒይ በሁለተኛው ሐዲስ አልሰሩበትም። ምክንያታቸው ሐዲሱ ከመጀመሪያው ሐዲስ ዝቅ ያለ ደረጃ ያለው መሆኑ ነው። የሻፊዒይን ሃሳብ የበይሀቂይ ዘገባ ያጠናክረዋል። የአላህ መልክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡-

إذا صمْتم فاستاكُوا بالغَداة ولا تَستاكُوا بالعَشِيّ

“ጥርሳችሁን ከፋቃችሁ በጧት አድርጉት። ከሰዐት በኋላ አትፋቁ።”

ነገርግን ከሻፊዒይ ውጪ ያሉት ሦስቱ ኢማሞች -ማሊክ፣ አቡ ሐኒፋና አሕመድ- “በማንኛውም ሁኔታ ጾመኛ ጥርሱን መፋቁ አይጠላበትም። ጸሀይ ወደ ምዕራብ ከመዘንበሏ በፊትም ሆነ በኋላ ጥርስን መፋቅ አይከለከልም።” ብለዋል።

ማስረጃቸው ዓሚር ኢብኑ ረቢዐህ ያስተላለፉት ከላይ የጠቀስነው ሐዲስ ነው። የጾመኛን የአፍ ጠረን የሚያወድሰው የመጀመሪያውን ሐዲስ በጾም ለማበረታታት የተነገረ ንግግር እንደሆነ ነው የተረዱት። ጾም የአፍን ጠረን ማበላሸቱ ሰዎችን ከመጾም እንዳያግዳቸው የተነገረ ሐዲስ ነው እንጂ ጠረኑ እንዲቆይና እንዳይጠፋ እንድናደርገው የሚያዝ ወይም የሚያበረታታ መልእክት የለውም።

ከዚያም እነዚህ ኢማሞች እንዲህ አሉ፡- መጥፎው የአፍ ጠረን ተደጋግሞ በሚሰራው ለዉዱእ በመጉመጥመጥ ይጠፋል። ነገርግን አትጉመጥመጡ የሚል ክልከላ አልተዘገበም። ከላይ የተጠቀሰው የበይሀቂይ ሐዲስ ደግሞ ደካማ ነው። ይህንንም እራሳቸው በይሀቂይ ተናግረዋል።

ጾመኛ ከዙህር ወቅት በኋላ ጥርሱን መፋቅ የለበትም ያሉት -ከአራቱ ኢማሞች መሀል- ሻፊዒይ ብቻ ከመሆናቸው ጋር የመዝሀባቸው ትልልቆቹ ልሂቃን ደግሞ የርሳቸውን አቋም አልወደዱም።

ነወዊይ -ትልቁ የሻፊዒይ መዝሀብ ልሂቅ- አል-መጅሙዕ የተሰኘው መፅሐፋቸው -ቅፅ 1፣ ገፅ 39- ላይ እንዲህ ይላሉ፡- “ለጾመኛ በማንኛውም ወቅት ጥርስን መፋቅ አለመጠላቱ የተሻለው አቋም ነው።”

የሻፊዒይን ንግግር ተከትለው ኢማም ኢብኑ ደቂቅ እንዲህ ብለዋል፡- “የጾመኛን የአፍ ጠረን የሚያወድሰውን ሐዲስ ጥቅል መልእክት የሚገድብ -ጸሀይ ወደ ምዕራብ ከተዘነበለ በኋላ ብቻ ጥርስን መፋቅ መከልከሉን የሚያመለክት- ልዩ መረጃ ያስፈልጋል። ስለዚህ በረመዳን በማንኛውም ቀውት ጥርስን መፋቅ አይጠላም።”

በጾም ውስጥ ሲዋክን/መፋቂያን መጠቀምን አስመልክቶ የተነገሩ ሃሳቦች እንዳሉ ሆነው ግን የአብዝሃኞቹ ዑለሞች ሃሳብ የተሻለ እንደሆነ እናምናለን። ጥርስን በማንኛውም መንገድ በማንኛውም ወቅት ማፅዳት አይጠላም። ነገርግን ጥርሱን ለማፅዳት የሚጠቀምባቸው ኬሚካሎችም ሆኑ ደም ወደ ሆዱ እንዳይገባ መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ለመጠንቀቅ የሚያስቸግሩ ነገሮችን የሚጠቀም ከሆነ ደግሞ በሌሊት ማድረጉ የተሻለ ነው።

አላህ የበለጠ ያውቃል!