በረመዳን አውቆ ጾምን ማፍረስ ብይኑ ምንድን ነው?

Home የፈትዋ ገጽ ዒባዳ ጾምና ኢዕቲካፍ በረመዳን አውቆ ጾምን ማፍረስ ብይኑ ምንድን ነው?

ጥያቄ፡- አጎቴ እኔ ቤት ውስጥ ይኖራል። ረመዳንን አይጾምም። ሆን ብሎ እያወቀ ያፈጥራል። እኔ ምንድን ነው ማድረግ ያለብኝ? ባለቤቴ ምግቡን በመስራቷ ኃጢያተኛ ትሆናለች?


መልስ፡- ጾም ግዴታ መደረጉን ከድቶ ከሆነ ከኢስላም ይወጣል። ይከፍራል። በረመዷን የሚያፈጥረው -አውቆ፣ ያለበቂ ሸሪዓዊ ምክንያት እና እርም መሆኑን እያመነ ከሆነ ሙስሊም ነው፤ ከኢስላም አይወጣም። ነገርግን እጅግ ከባድ ኃጢያት ፈፅሟል። አመጸኛ ነው። ቅጣትም ይገባዋል። በሁሉም ዑለሞች ስምምነት መሰረት ያመለጠውን ቀዷ መክፈል ግዴታ ይሆንበታል። በኢምም አሕመድ መዝሀብ እና በሻፊዒይም አንዱ አቋም መሰረት ከዚህ ውጪ ሌላ መቀጫ የለበትም። በሁለቱ ኢማሞች- በአቡሐኒፋ እና በኢማም ማሊክ- እንዲሁም በሻፊዒይ ሌላኛው አቋም መሰረት ደግሞ ከቀዷው በተጨማሪ መቀጫ (ከፋራ) ግዴታ ይሆንበታል። ይህንን የዑለሞች አቋም በይበልጥ እንደግፋለን። አውቆ ያፈጠረ ሰው መቀጫ እንደ ዚሃር መቀጫ ነው። አላህ እንዲህ ብሎ ገልጾታል፡-

وَالَّذِينَ يُظَاهِرُونَ مِن نِّسَائِهِمْ ثُمَّ يَعُودُونَ لِمَا قَالُوا فَتَحْرِيرُ رَقَبَةٍ مِّن قَبْلِ أَن يَتَمَاسَّا ۚ ذَٰلِكُمْ تُوعَظُونَ بِهِ ۚ وَاللَّهُ بِمَا تَعْمَلُونَ خَبِيرٌ * فَمَن لَّمْ يَجِدْ فَصِيَامُ شَهْرَيْنِ مُتَتَابِعَيْنِ مِن قَبْلِ أَن يَتَمَاسَّا ۖ فَمَن لَّمْ يَسْتَطِعْ فَإِطْعَامُ سِتِّينَ مِسْكِينًا ۚ ذَٰلِكَ لِتُؤْمِنُوا بِاللَّهِ وَرَسُولِهِ ۚ وَتِلْكَ حُدُودُ اللَّهِ ۗ وَلِلْكَافِرِينَ عَذَابٌ أَلِيمٌ

“እነዚያም ከሚስቶቻቸው እንደናቶቻችን ጀርባዎች ኹኑብን በማለት የሚምሉ ከዚያም ወደ ተናገሩት የሚመለሱ ሳይነካኩ በፊት ጫንቃን ነጻ ማውጣት በነርሱ ላይ አለባቸው። እነሆ በእርሱ ትገሰጹበታለችሁ። አላህም በምትሠሩት ሁሉ ውስጥ ዓዋቂ ነው። ያላገኘም ሰው ከመነካከታቸው በፊት ሁለት የተከታተሉ ወሮችን መጾም አለበት። ያልቻለም ሰው ስድሳ ድኾችን ማብላት (አለበት)። ይህ በአላህና በመልክተኛው እንድታምኑ ነው። ይህችም የአላህ ሕግጋት ናት። ለከሓዲዎችም አሳማሚ ቅጣት አልላቸው።” (አል-ሙጃዳላ 58፤ 3-4)

ማንም ሰው ደግሞ ሌላን ሰው በኃጢያት ላይ ማገዝ የለበትም። ስለዚህ ባለቤትህ ምግብ ማዘጋጀት አይፈቀድላትም። ይልቁንስ ከሁላችሁም የሚጠበቀው ነገር ኃጢያቱ እንዳይፈፀም መከላከል ነው።

እኛንም ሆነ ሰውየውን ወደ መንገዱ እንዲመራን፣ ተውበት እንዲለግሰን እና በዲኑ ህጎች እምንሰራ እንዲያደርገን እንለምነዋለን።

አላሁ አዕለም!