በረመዳን መቀማጠል

Home የፈትዋ ገጽ ጾምና ኢዕቲካፍ በረመዳን መቀማጠል

ጥያቄ፡- በረመዳን ፊልሞችን መመልከት እና ዘፈን መስማት ብይኑ ምንድን ነው?


መልስ፡- ቢስሚላሂር-ረሕማኒር-ረሒም። አልሐምዱሊላሂ ረቢል-ዐለሚን። ወስ-ሶላት ወስ-ሰላም ዓላ ረሱሊላህ ወበዕድ፡-

በጥቅሉ ፊልምና ቲያትሮችን መመልከትና ዘፈንን መስማት ብይን በነዚህ መስፈርቶች ይቃኛል፡- የሚታዩና የሚደመጡ የ “ጥበብ” ውጤቶች የተበከለ ንግግር ካዘሉ፣ ወደ ሐራም ከተጣሩ፣ አስተሳሰብና ጠባይ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ካላቸው፣ ከግዴታዎች ካዘናጉ ወይም እርም የሆነ ነገር ከተቆራኛቸው -ለምሳሌ፡- አልኮል መጠጥ፣ ወንድና ሴቶች መቀላቀል (ኢኽቲላጥ)…- እርም ይሆናሉ። ይህ ረመዳንን ከሌሎች ወራት የማይለይ ጥቅል ብይን ነው። ነገርግን ከነዚህ ክልክል ነገሮች ከፀዱ ማብዛቱ ይጠላል እንጂ -ራስን ትንሽ ዘና ለማድረግ- በጥቂቱ መመልከት ወይም ማዳመጥ አይከለከልም።

የረመዳን ወር የተለየ ጠባይ አለው። ነፍስን በማቀብ፣ አዕምሮን እና ስሜትን መቆጣጠር ለመልመድ የሚያስችል ልዩ ባህሪ አለው። ይህም መብላት፣ መጠጣትና የግብረ ሥጋ ስሜትን በመተው ብቻ አይገደብም። መብላት፣ መጠጣትና ግብረ-ሥጋን መተው አነስተኛው የጾም ደረጃ ነው። በጥቂት ምንዳ ተብቃቅተው ከአላህ ቅጣት ለመዳን ብቻ የሚጾሙት ተራ ሰዎች ብቻ ናቸው እንዲህ ብቻ የሚጾሙት።  ሌሎቻቸው ግን አምልኮኣቸው የተሟላ እና የላቀ እንዲሆን ይተጋሉ። ሁሉንም ዓይነት ስሜት ለማቀብ ይጥራሉ። በተለይም አላህ እርም ካደረጋቸው ሐሰትና ሐሜትን ከመሰሉ ተግባራት ይርቃሉ። እንደውም አንዳንዶቹ -በመንፈሳቸው ይመጥቁና- የተፈቀዱ ስሜቶቻቸውን እስከመተው ይደርሳሉ። በዚህ ወር ውስጥ በተለይ በሁለመናቸው ወደ አላህ ይዞሩና መንፈሳቸውን እና ጠባያቸውን ከቆሻሻ ለማፅዳት ይተጋሉ። ታላላቅ ባህሪያትን ለመላበስ ይታትራሉ።

የዚህ ወር ትሩፋት እንዳያመልጥ መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ወሩ ምንዳዎች የሚነባበሩበትና ምህረት የሚታደልበት ወር ነው። ቀኑን በአግባቡ መጾም እና ለሊቱንም በሶላት እና ቁርኣንን በማንበብ ማሳለፍ ተገቢ ነው። ቲያትር ወይም ፊልሞችን በመመልከት ጊዜ ማቃጠል ህሊና ላለው ሙእሚን ኪሳራ ነው። ስለዚህ ኃላፊነት የሚሰማው ሰው ሁሉ የዚህን ወር ክብር እንዲጠብቅ እናሳስባለን። ለጾመኞች የሚመች አየርን -በቤት ውስጥ- መፍጠር ያስፈልጋል። በጨዋታና በዛዛታ መጠመድ አይገባም። ጊዜን በአግባቡ መጠቀም ብልህነት ነው።

ምንም ይሁን ግን እነዚህ ተግባራት -ለግብረ-ሥጋ ውጤቶች እስካልዳረጉ ድረስ- ጾምን አያፈርሱም። ጾሙ ባይበላሽም ቅሉ በአኺራው ሀገር ትርፋማ ያደርግ የነበረውን ውዱን ጊዜ ያለ አግባብ መጠቀም በራሱ ጥፋትና ኪሳራ ነው። ቤት ውስጥ -ከኢስላማዊ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ውጪ ያሉትን ማጥፋት ይመከራል። ጊዜው ውድ ነው። ወደ አላህ የምንዞርበት፣ የአመቱን ኃጢኣታችንን የምናስምርበት ወርቃማ ወቅት ነው። የአላህ መልክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡-

أتاكم رمضان شهر بركة، يغشاكم الله فيه فيُنزل الرحمة، ويحُطُّ الخطايا، ويستجيب فيه الدعاء، ينظر الله إلى تنافسكم فيه ويباهي بكم ملائكته، فأروا الله من أنفسكم خيرًا؛ فإن الشقي من حرم به رحمة الله عز وجل

“ረመዳን መጣላችሁ። የበረከት ወር ነው። በርሱ ውስጥ አላህ ይቀርባችኋል። እዝነቱም ይወርዳል። ኃጢኣትንም ይሰርያል። ዱዓንም ይቀበላል። በርሱ ውስጥ ለመልካም ተግባር የምታደርጉትን እሽቅድድም ይመለከታል። በመላእክት ላይም በናንተ መልካም ነት ይፎክራል። ከነፍሶቻችሁ ለአላህ መልካምን አሳዩት። መናጢ ማለት በረመዳን የአላህን እዝነት የተነፈገ ሰው ነው።”

የረመዳን ፉክክር በዛዛታና በጨዋታ ሳይሆን በመልካም ሥራዎች እና ነፍስን በማፅዳት ላይ ይሁን!!!