ሶደቃን በሚስጥር መስጠት ይሻላል ወይስ በይፋ?

Home የፈትዋ ገጽ ማህበራዊ ጉዳዮች ሶደቃን በሚስጥር መስጠት ይሻላል ወይስ በይፋ?

ጥያቄ፡- ሶደቃን በሚስጥር መስጠት ይሻላል ወይስ በይፋ?


መልስ፡- የመልካም ሥራዎች መዘውር ኢኽላስ ነው። መልካም ሥራ መልካም ነው የሚባለው ኢኽላስ ሲኖረው ነው። ስለዚህ ሰውየው ልታይ ባይነት (ሪያእ) ይፈጠርብኛል ብሎ ከፈራ በይፋ ከሚደረግ ምጽዋት በሚስጥር የሚደረገው የተሻለ ነው። የዐርሽ ጥላ እንጂ ሌላ ጥላ በሌለበት የትንሳዔ ቀን ከዐርሽ ጥላ ሥር ከሚሆኑት ሰባት ሰዎች መሀል “ምጽዋት ሲሰጥ ቀኙ የምትሰጠውን ግራው እንዳታውቅ አድርጎ የሰጠ ሰው” ይገኛል። ይህ ሐዲስ የሚጠቁመው ያስቀደምነውን ሃሳብ ነው።

በመሆኑም ሰውየው ሪያእ ላይ እወድቃለሁ የሚል ስጋት ከሌለውና ሰዎች አርዓያውን ተከትለው እንዲመጸውቱ ለማድረግ አስቦ እስከሆነ ድረስ በይፋ የሚሰጠው ምጽዋት ከድብቁ ይሻላል። ይህ የአል-ዑስራን ዘመቻ ለመደጎም የተደረገው ውድድር ላይ ታይቷል። የአላህ መልክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) አንድ ሰው ራሱን ከሰዎች በልጦ ለማግኘት ሲል ሌላ ሰው ከለገሰው በላይ መስጠቱን አላነወሩም። እንደውም አንዳንዶቹ ሰዎች ከራሳቸው በላይ የሚሰጥ ሰው አይኖርም ብለው አስበው ሶድቀው የሚበልጣቸው ሰው መኖሩን አግኝተዋል። አቡበክር ሲዲቅ (ረ.ዐ) ከሁሉም በልጠው ተገኝተዋል። ያላቸውን ኃብት በሙሉ ለግሰዋል። ለቤተሰቦቻቸው አላህና መልክተኛውን ትተዋል። ዑመር ተፎካካሪያቸው ነበሩ። ግማሽ ኃብታቸውን ለግሰው ሲያበቁ “አቡ በክርን ከበለጥኩኝ የምበልጠው ዛሬ ነው!” ብለው ነበር።

ሶሐቦች ከሙዶር የመጡትን ድሆች ለማቋቋም በተደረገው መዋጮ ላይም ተወዳድረው ነበር። የአላህ መልክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) በዚያን ወቅት ተከታዩን ተናግረዋል፡-

مَن سنَّ سُنة حسنة فله أجرُها وأجْر مَن عَمِل بها إلى يوم القيامة

“በኢስላም ውስጥ በአርዓያነቱ የሚያስመሰግንን በጎ ጅምር ያሳየ ሰው የራሱና እስከ ምጽዓት ቀን ድረስ በርሱ ፈለግ ተከትለው የሰሩ ሰዎችን ምንዳም ያገኛል።”

አላህ እንዲህ ብሏል፡-

إِن تُبْدُوا الصَّدَقَاتِ فَنِعِمَّا هِيَ ۖ وَإِن تُخْفُوهَا وَتُؤْتُوهَا الْفُقَرَاءَ فَهُوَ خَيْرٌ لَّكُمْ
“ምጽዋቶችን ብትገልጹ እርሷ ምንኛ መልካም ናት፡፡ ብትደብቋትና ለድኾች ብትሰጧትም እርሱ ለናንተ በላጭ ነው፡፡” (አል-በቀራ፣ 271)

ኢማም አል-ቁርጡቢይ የተፍሲር መጽሐፋቸው ላይ በዚች አንቀጽ ላይ የተሰነዘሩ አስተያየቶች ከጠቀሱ በኋላ እንዲህ ብለዋል፡- “ምጽዋትን ደብቆ በመስጠትና በይፋ በመስጠት ዙርያ ትክክለኛው ሃሳብ ጉዳዩ በሰጪው፣ በተቀባዩና በተመልካቾች ሁኔታ የተወሰነ መሆኑ ነው። ሰጩ በይፋ በመስጠቱ የመልካም አርዓያነትን ትሩፋት ሊያገኝ ይችላል። ነገርግን ኒያው ጠንካራ በመሆኑ በቀላሉ ለሪያእ የማይጋለጥ ከሆነ ነው። ነገርግን የንጽሕና ደረጃው ዝቅ ያለበት ሰው በድብቅ መስጠት ይሻለዋል።

ተቀባይ በድብቅ የሚሰጥ ምጽዋት ይሻለዋል። ሰዎች እንዳይንቁት ያደርገዋል። ለጉዳዮቹ የሚበቃው ንብረት እያለው በስግብግብነት ተነሳስቶ ገንዘብ የተቀበለ እንዳይመስላቸውና ክብሩን እንዳይነኩ ይጠብቀዋል።”

ከዚያም -አል-ኪያ አጥ-ጦበሪን በመጥቀስ- ቁርጡቢይ እንዲህ አሉ፡- “ይች አንቀጽ በማንኛውም ሁኔታ ምጽዋትን መደበቅ የተሻለ እንደሆነ ታመለክታለቸ።”

ቁርጡቢይ ሌሎች ሃሳቦችንም ጠቅሰዋል። ነገርግን -ከላይ እንዳልነው- ሰውየው የሚጠቅመውን ከራሱ ሁኔታ አንጻር ቢወስን መልካም ነው። ምጽዋት ግዴታም ሆነ ሱና ኢኽላስ ያስፈልገዋል። ያለ ኢኽላስ ገለባና ምንዳ የሌለው ከንቱ ልፋት ነው። ሪያእ ሺርክ ነው። መጠንቀቅ ያስፈልጋል።

አላህ የበለጠ ያውቃል!