ሶላት ውስጥ ከፋቲሐ ጋር ድምፅን ከፍ አድርጎ “ቢስሚላሂር-ራሕማኒር-ረሒም” ማለት

Home የፈትዋ ገጽ ሰላት ሶላት ውስጥ ከፋቲሐ ጋር ድምፅን ከፍ አድርጎ “ቢስሚላሂር-ራሕማኒር-ረሒም” ማለት

ጥያቄ፡- ድምጽን ከፍ አድርጎ በሚሰገድባቸው ሶላቶች ውስጥ ፋቲሐን ስንቀራ ድምፅን ከፍ አድርጎ ቢስሚላሂ ማለት ግዴታ ነው? ስለዚህ ድምፁን ከፍ አድርጎ የማያነባትን ሰው ተከትለን አንስገድ ወይስ ድምፅን ከፍ ማድረግም ሆነ ዝግ ማድረግ እኩል ነው?


መልስ፡- በሶላት ውስጥ “ቢሰሚላሂን…” ከፍ ባለ ድምፅ ማንበብ (አል-ጃህር ቢበስመላህ) ዑለሞች የተለያዩበት ጉዳይ ነው። ሻፊዒዮቹ ድምፅን ከፍ ማድረግ ሱና ነው ብለው ያምናሉ። ሌሎች ዑለሞች ደግሞ ድምፅን ዝግ አድርጎ እርሷን ማንበብ ይሻላል ይላሉ። ይህ ድርጊት ከሶላት ጌጦች (ሐይኣት) መሀል የሚቆጠር ስራ ነው። ጥብቅ ሱና አይደለም። በዑለሞቹ መሀል ያለውም ልዩነት ቀላል ነው። ነገሩም ሰፊ ነው። ሰዎች ተቃራኒያቸውን ማውገዝ ወይም መቃወም የሚችሉት ስምምነት ባለባቸው ጉዳዮች ላይ ብቻ ነው። የዑለሞች ልዩነት ያለበት ጉዳይ ላይ ሰዎችን መቃወም አይፈቀድም።

ቢስሚላሂን ድምፁን ከፍ አድርጎ ያነበበ ሰው ችግር የለበትም። በልቡ ያነበባት ሰው ሶላትም እንከን የለውም። በዚህ መሰል ልዩነቶች ፈተና ማስነሳትና መጨቃጨቅ ተገቢ አይደለም። የሙስሊሞችንም አንድነት ይበታትናል። ስለዚህ ምርጥ የሰለፍ አባቶቻችን በነበሩበት ሁኔታ የልዩነት አደብ ተላብሰን በሰላምና በመግባባት መተዳደር አለብን።

አላሁ አዕለም!