ስልጣንን አስታኮ የህዝብን ኃብት ለግል ጥቅም ማዋል

Home የፈትዋ ገጽ ማህበራዊ ጉዳዮች ገንዘብ ነክ ስልጣንን አስታኮ የህዝብን ኃብት ለግል ጥቅም ማዋል

ጥያቄ፡- እባካችሁን አንዳንድ የመንግስት ወይም የግል ድርጅት ሰራተኞች -በተለይም ኃላፊዎች- ስልጣናቸውን በመጠቀም የሚያካብቱት ኃብት ላይ ያለው ሸሪዐዊ አቋም ምን እንደሆነ አስረዱን?


መልስ፡- የህዝብ ኃብት ማለት -የፊቅህ ልሂቃን ዘንድ- ባለቤቱ ያልተለየ በሀገር ውስጥ የተገኘ የሀገሪቱ ህዝቦች ንብረት ነው። አል-ቃዲ አል-ማወርዲይና ቃዲ አቡ የዕላ እንዲህ ይላሉ፡- “የህዝብ ኃብት ማለት ባለቤቱ ውስን ያልሆነ ሁሉም የህዝብ የሆነ ኃብት ነው።” (አል-መውሱዐቱል-ፊቅሂያ፣ ቅፅ 8፣ ገፅ 242)

በኢስላም የህዝብ ገንዘብ የህዝብ እንጂ በኃላፊነት የሚመደቡ አስተዳዳሪዎች ኃብት አይደለም።  በኢስላማዊው አስተዳደር ውስጥ ያለ ኸሊፋም፣ አሚርም ይሁን ፕሬዝዳንት ንብረት አይደለም።

በአቡሁረይራ ሐዲስ ውስጥ የተዘገበው መልእክት ይህንን ያሳያል።  የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ይላሉ፡-

ما أعطيكم ولا أمنعكم، إنما أنا قاسمٌ، أضعُ حيث أُمرت

“እኔ አልሰጠኋችሁም፤ አልከለክላችሁምም።  እኔ አካፋይ ነኝ።  ገንዘብን የታዘዝኩበት ቦታ ላይ አኖረዋለሁ።” ቡኻሪይ ዘግበውታል።

በሌላ ዘገባ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ይላሉ፡-

ما أُوتيكم من شيءٍ وما أمنعكموه، إن أنا إلا خازنٌ، أضع حيث أُمرت

“የተሰጣችሁን ነገር እኔ አልከለክላችሁም።  እኔ ካዝና ጠባቂ ነኝ።  ገንዘብን በታዘዝኩበት አደርገዋለሁ።” አቡዳዉድ ዘግበውታል።

አል-ሐፊዝ ኢብኑ ሐጀር እንዲህ ይላሉ፡- “የተሰጣችሁን ነገር እኔ አልከለክላችሁም” ከሹረይሕ ቢን ኑዕማን ከፉለይሕ በተዘገበ ሌላ ዘገባ ላይ “አላህ ነው የሚሰጠው” የሚል ጭማሪ አለ። ትርጉሙም በግል ፍላጎቴ የመስጠትም ሆነ የመከልከል ስልጣን የለኝም። “እኔ አካፋይ ነኝ” ማለት ለታዘዝኩት አካል እሰጣለሁ ማለት ነው። በአላህ ትዕዛዝ እንጂ አልሰጥም፤ አልከለክልም ማለትም ነው። አቡዳዉድ ሃማምን ጠቅሰው ከአቡሁረይራ ዘግበውታል።  (ፈትሑል-ባሪ፣ ቅፅ 6፣ ገፅ 218)

ይህ ሐዲስ የህዝብ ገንዘብ የህዝብ እንጂ የባለስልጣን አለመሆኑን ያስረዳል።  ሸይኹል-ኢስላም ኢብኑ ተይሚያ እንዲህ ይላሉ፡- “ተከታዩ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ንግግር፡-

إني والله لا أُعطي أحداً، ولا أَمنع أحداً، وإنما أنا قاسمٌ أضع حيث أُمرت

“እኔ -ወላሂ- ማንንም ሰው አልሰጥም፤ አልከለክልምም።  እኔ የታዘዝኩበት ቦታ የማኖር አካፋይ ብቻ ነኝ።” ይህ ሐዲስ ባለስልጣን የህዝብ ኃብት ባለቤት ሊሆን እንደማይችል ያስረዳል።” (ሚንሃጁስ-ሱን-ነቲን-ነበዊያ፣ ቅፅ 6፣ ገፅ 218)

አሁንም ሼኹል-ኢስላም ኢብኑ ተይሚያ እንዲህ ይላሉ፡- “የሙስሊሞች መሬት ጥቅም ለሙስሊሞች አጠቃላይ ጥቅም መዋል አለበት። መንግስት ለባለመብቶች ሐቃቸውን አካፋይ እንጂ ትውስት ወይም ስጦታ እንደሚሰጥ አካል ‘ውለተኛ’ (በፍቃደኝነቱ ውለታ የሚውል) አይደለም።” (አል-ሑስባ፣ ገፅ 40)

ኢብኑ ዘንጁዊየህ ከማሊክ ኢብኑ አውስ ሲዘግቡ እንዲህ ይላሉ፡-

“አንድ ቀን ዑመር ኢብኑል-ኸጧብ ፈይእን (ያለውጊያ ከጠላት የሚገኝን ንብረት) አነሱና እንዲህ አሉ፡- ‘ምን ሆናችሁ ነው ሰዎች ሆይ የማትነጋገሩት።  ወላሂ እኔ በዚህ ገንዘብ ላይ ከናንተ የበለጠ መብት የለኝም።  አንዳችንም ከሌላው የሚበልጥ መብት አይኖረውም።  ሁላችንም የአላህ መፅሀፍና የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ባካፈሉን መሠረት እንካፈላለን። ሰውየው በኢስላም ውስጥ ያለው ቆይታ፣ የከፈለው መስዋእትነት፣ የቤተሰቡ ሁኔታ እና አስፈልጎቱን ያገናዘበ አከፋፈል እንከተላለን።  ማንኛውም ሙስሊም ከዚህ ገንዘብ ሐቅ አለው።  ቢሰጠውም ቢከለከልም ይህን መብቱን አይገፈፍም። … እድሜዬ ከቆየም በሰንዐእ ተራራ ላይ ሆኖ ከብቶች የሚያግደው እረኛ እንኳን ሳይቀር ከአላህ ፈይእ የድርሻውን ያገኛል።” (አል-አምዋል የተሰኘው የኢብኑ ዘንጀዊየህ መፅሀፍ፣ ቅፅ 2፣ ገፅ 284)

አቡ ዑበይድ ኢብኑል-ቃሲም -ከዐጢያ ኢብኑ ቀይስ ይዘው- እንዲህ ይላሉ፡- “ሙዐዊያ ኹጥባ አደረጉ።  ከዚያም እንዲህ አሉ፡- ‘የገንዘብ ቤታችሁ ውስጥ ትርፍ ገንዘብ ካለ እሰጣችኋለሁ። እኔ በመሀላችሁ አካፋይ ነኝ። በሚመጣው አመት ላይ ገንዘብ ካለ ለናንተው አካፍላለሁ። ከሌለም ግን እኔ አልወቀስም። እርሱ የኔ ገንዘብ አይደለም። አላህ ለናንተ የሰጠው ገንዘብ ነው።” (አል-አምዋል የተሰኘው የአቡ ዑበይድ መፅሀፍ ላይ፣ ቅፅ 2፣ ገፅ 84 ላይ ዘግበውታል።)

ሸይኽ ኢብኑ ቁዳማ እንዲህ ይላሉ፡- “የገንዘብ ቤት (በይቱል-ማል) ኃብት የሙስሊሞች ሁሉ ነው።  ኢማሙ ማድረግ የሚችለው ለሚገባቸው አካላት እንዲደርስ ማመቻቸት ብቻ ነው።” (አል-ሙግኒ ቅፅ 6፣ ገፅ 204)

ሸይኹል-ኢስላም ኢብኑ ተይሚያ እንዲህ ያላሉ፡- “መንግስታት አንድ ሰው የግል ገንዘቡን እንደሚያካፍለው የህዝብን ገንዘብ በራሳቸው ፍላጎት ማከፋፈል አይችሉም። እነርሱ አደራ ተቀባይ ወይም ወኪሎች ናቸው። የገንዘቡ ባለቤቶች አይደሉም። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ይላሉ፡-

إني والله لا أُعطي أحداً ولا أمنع أحداً، وإنما أنا قاسمٌ أضع حيث أُمرت

‘እኔ -ወላሂ- ለማንም አልሰጥም፤ አልከለክልምም። እኔ አካፋይ ነኝ፤ የታዘዝኩበት ቦታ ላይ ነው የማኖረው።’ ቡኻሪይ ዘግበውታል።” (መጅሙዑ ፈታዋ ሸይኺል-ኢስላም ቅፅ 6፤ ገፅ 372)

ሸውካኒይ እንዲህ ይላሉ፡- “በይቱል-ማል የሙስሊሞች ገንዘብ ግምጃ ቤት ነው። ባለቤቶቹ እነርሱው ናቸው።” (አስ-ሰይሉል-ጀራር ቅፅ 3፣ ገፅ 333)

በዚህ መሰረት የንጉስ ስጦታ፣ የፕሬዝዲያንሻል ስጦታ ወይም የአሚር ስጦታ የሚባል ነገር -በኢስላም- የለም ማለት ነው። ስጦታው ከግል ኪሱ ከሆነ ብቻ ነው ስጦታ የሚባለው። ከህዝብ ገንዘብ የሚሰጥ ስጦታ የለም። መብቱ ለሆነ አካል ይሰጣል። መብቱ ያልሆነው ወገን ደግሞ ይከለከላል። ፕሬዝዳንቱ፣ መቅላይ ሚኒስትሩ፣ አሚሩ ወይም ኸሊፋው ግን እንደማንኛውም ሰው ከራሱ ገንዘብ ለሰዎች ሊሰጥ ይችላል። በህዝብ ገንዘብ ላይ እንዳሻው የማዘዝ መብት ግን የለውም።

ይህ በደምብ ከተረጋገጠ ወደ ጥያቄው እንመለሳለን፡-

አንደኛ፡- ሰራተኛ ወይም ኃላፊ -ደረጃው- ትንሽም ይሁን ትልቅ ቅጥረኛ ነው። ቅጥረኛ ደግሞ ታማኝ መሆን አለበት። የተሰጠው የስራ ድርሻ አማና ነው። ይህ የህዝብ አገልግሎት ላይ ያሉ ሰዎችንና የህዝብ ገንዘብንም ይመለከታል። የህዝብን ገንዘብ መጠበቅና በሚገባው መልኩ ማስተዳደር ግዴታ ነው። አላህ እንዲህ ይላል፡-

قَالَتْ إِحْدَاهُمَا يَا أَبَتِ اسْتَأْجِرْهُ إِنَّ خَيْرَ مَنِ اسْتَأْجَرْتَ الْقَوِيُّ الْأَمِينُ

“ከሁለቱ አንደኛይቱም ‘አባቴ ሆይ ቅጠረው፡፡ ከቀጠርከው ሰው ሁሉ በላጩ ብርቱው ታማኙ ነውና’ አለችው፡፡” (ቀሷስ፣ 26)

በሌላ አንቀፅም አላህ እንዲህ ይላል፡-

إِنَّ اللَّهَ يَأْمُرُكُمْ أَن تُؤَدُّوا الْأَمَانَاتِ إِلَىٰ أَهْلِهَا وَإِذَا حَكَمْتُم بَيْنَ النَّاسِ أَن تَحْكُمُوا بِالْعَدْلِ إِنَّ اللَّهَ نِعِمَّا يَعِظُكُم بِهِ إِنَّ اللَّهَ كَانَ سَمِيعًا بَصِيرًا

“አላህ አደራዎችን ወደ ባለቤቶቻቸው እንድታደርሱ ያዛችኋል፡፡ በሰዎችም መካከል በፈረዳችሁ ጊዜ በትክክል እንድትፈርዱ (ያዛችኋል)፡፡ አላህ በርሱ የሚገሥጻችሁ ነገር ምን ያምር! አላህ ሰሚ ተመልካች ነው፡፡” (ኒሳእ፣ 58)

በሌላም አንቀፅ እንዲህ ይላል፡-

وَالَّذِينَ هُمْ لِأَمَانَاتِهِمْ وَعَهْدِهِمْ رَاعُونَ

“እነዚያም እነርሱ ለአደራዎቻቸውና ለቃል ኪዳናቸው ጠባቂዎች፡፡” (ሙእሚኑን፣ 8)

በሌላም አንቀፅ እንዲህ ብሏል፡-

يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا لَا تَخُونُوا اللَّهَ وَالرَّسُولَ وَتَخُونُوا أَمَانَاتِكُمْ وَأَنتُمْ تَعْلَمُونَ

“እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አላህንና መልክተኛውን አትክዱ፡፡ አደራዎቻችሁንም እናንተ እያወቃችሁ አትክዱ፡፡” (አል-አንፋል፣ 27)

አቡ ዘር እንዲህ ይላሉ፡- “የአላህ መልእክተኛ ሆይ አይሾሙኝም?!” አልኩኝ።  እርሳቸውም በእጃቸው ትከሻዬን መቱኝና ‘አቡዘር ሆይ አንተ ደካማ ነህ።  እርሷ (ሹመት) ደግሞ አማና ናት።  በአግባቡ ከያዛትና ያለበትን ኃላፊነት ከተወጣ ሰው በስተቀር የቂያማ ቀንም ውርደትና ፀፀት ትሆናለች።’ አሉኝ” ሙስሊም ዘግበውታል።

ሁለተኛ፡- በህዝብ ገንዘብን ማባከን አስከፊ ኃጢያት መሆኑን የሚጠቁሙ ብዙ አንቀፆች አሉ።  አላህ እንዲህ ይላል፡-

وَلَا تَأْكُلُوا أَمْوَالَكُم بَيْنَكُم بِالْبَاطِلِ وَتُدْلُوا بِهَا إِلَى الْحُكَّامِ لِتَأْكُلُوا فَرِيقًا مِّنْ أَمْوَالِ النَّاسِ بِالْإِثْمِ وَأَنتُمْ تَعْلَمُونَ

“ገንዘቦቻችሁንም በመካከላችሁ በከንቱ (ያለ አግባብ) አትብሉ፡፡” (አል-በቀራ፣ 188)

በሐዲስ ውስጥ ከአቡ ሰዒድ አል-ኹድሪይ እንደተዘገበው የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ይላሉ፡-

إن هذا المال خضرة حلوة فمن أخذه بحقه ووضعه في حقه فنعم المعونة هو، ومن أخذه بغير حقه كان كالذي يأكل ولا يشبع

“ይህ ገንዘብ (ውስጡ ካለው ጌጥና አካላዊ ጥቅም አንፃር) አረንጓዴና ጣፋጭ ነው።  በአግባቡ ይዞት በሚገባው መልኩ ያወጣው ሰው እንዴት ዓይነት ረዳት ይሆናል!… ያለአግባብ የያዘው ሰው ግን እየበላ እንደማይጠግብ ሰው ነው።” ቡኻሪይ እና ሙስሊም ዘግበውታል።

ከአቡ ሰዒድ አል-ኹድሪይ እንደተዘገበው የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ይላሉ፡-

وإنه من يأخذه بغير حقه كان كالذي يأكل ولا يشبع، ويكون عليه شهيداً يوم القيامة

“ገንዘብን ያለአግባብ ያካበተው ሰው እየበላ እንደማይጠግበው ሰው ነው።  የቂያም ቀንም ምስክር ይሆንበታል!” ሙስሊም ዘግበውታል።

ከኸውላ አል-አንሷሪያ እንደተዘገበው የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ሲሉ ተሰምተዋል፡-

إن رجالاً يتخوضون في مال الله بغير حق فلهم النار يوم القيامة

“አላህን ገንዘብ -ያለ አግባብ- የሚጠቀሙ ሰዎች አሉ።  ለነርሱ የቂያማ ቀን እሳት አላቸው።” ቡኻሪይ ዘግበውታል።

ኢማም ቡኻሪይ በሰነዳቸው ከአቡ ሑመይድ አስ-ሳዒዲይ እንደዘገቡት እንዲህ ይላሉ፡- “የአላህ ነብይ (ሰ.ዐ.ወ) የአዝድ ጎሳ ሰው የሆነ አንድ ሰውን ሾሙት።  ኢብኑል-ለተቢያህ ይባላል።  ዘካ እንዲያሰባስብ ነበር የሾሙት።  ከዚያም ሲመለስ ‘ይህ የናንተ ገንዘብ ነው።  ይህኛው ግን ስጦታ ተሰጥቶኝ ነው።’ ማለት ጀመረ።  ከዚያም የአላህ ነብይ (ሰ.ዐ.ወ) ሚንበር ላይ ወጡና አላህን በማመስገንና እርሱን በማወደስ ኹጥባ ጀመሩ።  ከዚያም እንዲህ አሉ፡-

ما بال العامل نبعثه فيأتي يقول: هذا لك وهذا لي؟ فهلَّا جلس في بيت أبيه وأمه فينظر أيهدى له أم لا؟ والذي نفسي بيده لا يأتي بشيء إلا جاء به يوم القيامة يحمله على رقبته إن كان بعيراً له رغاء أو بقرة لها خوار أو شاة تيعر…

“የላክነው ሹማችን ምን አግኝቶት ነው ሲመጣ ‘ይህ ላንተ ነው፤ ይህ የኔ ነው’ የሚለን?! ስጦታ ይሰጠው ወይም አይሰጠው ለማወቅ የአባቱ ወይም የእናቱ ቤት አይቀመጥም ነበር?! ነፍሴ በእጁ በሆነችው ጌታ እምላለሁ ምንም ነገር አይወስድም የቂያም ቀን በጫንቃው ተሸክሞት የሚመጣ ቢሆን እንጂ! ግመል ከሆነ እየጮኸ የግመል ድምፅ እያሰማ፣ ከብትም ከሆነ የከብት ድምፅ እያሰማ፣ ፍየልም ከሆነ እየጮኸ ተሸክሞት መምጣቱ አይቀርም።” ይህ ሐዲስ በሹመት ምክንያት የተገኘ ተሰሚነትን እና ስልጣንን ለራስ ጥቅም ማዋል ሐራም እንደሆነ በግልፅ ያስረዳል።

አቡሁረይራ እንዲህ ይላሉ፡- “የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) በመሀላችን ተነሱና ከግዳይ ገንዘብ መስረቅን (ጉሉልን) አነሱ። ጉዳዩ ከባድ እንደሆነም ገለፁ። እንዲህ አሉ፡-

لا ألفين أحدكم يوم القيامة على رقبته شاة لها ثغاء، على رقبته فرس له حمحمة، يقول يا رسول الله أغثني. فأقول: لا أملك لك شيئاً قد أبلغتك وعلى رقبته بعير له رغاء يقول يا رسول الله أغثني، فأقول لا أملك لك شيئاً قد أبلغتك، وعلى رقبته صامت فيقول يا رسول الله أغثني، فأقول لا أملك لك شيئاً قد أبلغتك …

“የቂያም ቀን አንዳችሁንም በትከሻችሁ የሚጮህ ውሻን ወይም ፈረስን ተሸክሞ እንዳላገኘውና ያ ረሱለላህ እርዱኝ! እንዳይለኝ። እኔ ላንተ ምንም አላደርግልህም፤ መልእክቱን -በእርግጥም አድርሼልህ ነበር እለዋለሁ። በጫንቃው የሚጮኽ ግመል ተሸክሞ እንዳላገኘውና ያረሱለላህ እርዳኝ እንዳይለኝ። ‘አኔ ላንተ ምንም አላደርግልህም! በእርግጥም መልእክቱን አድርሼልሃለሁ።’ እለዋለሁ። ብርና ወርቅም ተሸክሞ ሲመጣ እንዳላገኘውና ያ ረሱለላህ እርዳኝ እንዳይለኝ። …” ቡኻሪይ እና ሙስሊም ዘግበውታል።

ኢማም ነወዊይ እንዲህ ይላሉ፡- “…ይህ ሐዲስ የግዳይ ገንዘብን መስረቅ (ጉሉል) ሐራም መሆኑን ያሳያል። … ጉሉል በቋንቋ ትርጉሙ መክዳት ማለት ነው። ነገርግን አገልግሎት ላይ የሚውለው ከግዳይ ገንዘብ የሚደረግን ማጭበርበር ለማመልከት ነው። … የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እነዚህን ሁኔታዎች የሚያላብስ ስራ ሰርታችሁ እንዳላገኛችሁ እያሉ ነው። … ከአላህ ፍቃድ ውጪ ላማልድህና ምህረት ላሰጥህ አልችልም ማለታቸው ነው። ይህ ጉሉል እጅግ የከበደ ኃጢያት መሆኑን ያሳያል። ስለዚህ ሰውየው የከዳውን ገንዘብ መመለስ እንዳለበት የዑለሞች ስምምነት አለ።” (ሸርሑ አን-ነወዊይ ዐላ ሶሒሕ ሙስሊም ቅፅ 4፣ ገፅ 532)

አል-ሐፊዝ ኢብኑ ሐጀር ከአንዳንድ የዒልም ሰዎች እንዳጣቀሱት “ይህ ሐዲስ ተከታዩን አንቀፅ ይተረጉማል፡-

يَأْتِ بِمَا غَلَّ يَوْمَ الْقِيَامَةِ

“በጫንቃው ላይ ተሸክሞ ይመጣል ማለት ነው።” ከዚያም እንዲህ አሉ፡- “የሰረቀው ገንዘብ ከግመል የቀለለ ስለሆነ ከግመል ያነሰ ነገር ተሸክሞ ይመጣል ስለዚህ ዋጋው ቀላል የሆነ ነገር የሰረቀ ሰው ዋጋው ከፍተኛ የሆነውን ከሰረቀው ሰው ያነሰ ቅጣት እንዴት ይቀጣል አይባልም። ምክንያቱም እዚህ ሊገለፅ የተፈለገው በዚያ አስፈሪ ወቅት -በፍጥረታት ፊት- የሚገጥመውን ውርደት ነው። የሚሸከመውን ነገር ክብደትና ቅለት አይደለም።” (ፈትሑል-ባሪ ቅፅ 6፣ ገፅ 224)

ሌሎችንም የሐዲስ እና የቁርኣን መረጃዎችን ማንሳት ይቻላል። ነገርግን እናጠቃለው፡-

የህዝብ ገንዘብን መመዝበር የግለሰብ ገንዘብን ከመስረቅ የከፋ ነው። ምክንያቱም የህዝብን ገንዘብ መስረቅ ላይ ያሉት ኃላፊነቶች ብዙ ናቸው። ደግሞም ባለቤቶቹ ብዙ ስለሆኑ ከሳሾቹም ብዙ ይሆናሉ።

የህዝብን ገንዘብ መጠበቅ አስመልክቶ ቁርኣንና ሐዲስ ብዙ ብለዋል። አንዳንድ ዐሊሞች የህዝብን ገንዘብ -ከየቲም ገንዘብ ጋር አወዳድረውታል፤ እርሱን መስረቅ ያለውን ክብደት ለመግለፅ።

ስለዚህ የህዝብ አገልግሎት ላይ የሚቀጠሩ ሰራተኞችም ሆኑ ኃላፊዎች የህዝብን ኃብት ከመመዝበር የመቆጠብ ግዴታ አለባቸው። የህዝብን ገንዘብ ለመመዝበር ስልጣንን መጠቀምም ሐራም ነው። ዑለሞች -በአንድነት- ይህንን ተግባር ከካባባድ ኃጢያቶች (ከባኢር) መድበውታል።

ወላሁ አዕለም!