ሴቶች ስፖርት ሲሰሩ መከተል ያለባቸው ስርዐት

Home የፈትዋ ገጽ ማህበራዊ ጉዳዮች ጤናና ህክምና ሴቶች ስፖርት ሲሰሩ መከተል ያለባቸው ስርዐት

ጥያቄ፡- ሴት ስፖርት መስራት ትችላለች? መከተል ያለባት ወሳኝ መርሆችስ ምንድን ናቸው?


መልስ፡- ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን አካልን ለማጠንከርና ጤናን ለመጠበቅ ብሎ መከወን ወንድና ሴት የማይለያዩበት ጉዳይ ነው። የስፖርት ዓይነቱ ደግሞ ሸሪዓዊ ብይኑን ይወስናል። አካልን ለማጠንከር ወይም እንደ እግር ኳስ ያሉ አዝናኝ የሆኑ ስፖርቶችም ቢሆኑ ይፈቀዳሉ። እንደውም አንዳንዴ ግዴታ ሊሆኑ የሚችሉበት አጋጣሚ ሊፈጠርም ይችላል። ነገርግን በስፖርት እንቅስቃሴዎች ጊዜ ሃፍረተ ገላን መሸፈን ግዴታ ነው። ስፖርት እርም ከሆኑ የገንዘብ ልውውጦችም ውጪ መሆን አለበት። ለምሳሌ ቁማር ሊኖርበት አይገባም። ሴት በአለባበሷ ጥቅል የሆኑ የሸሪዓ ድንጋገዎችን በሙሉ መከተል አለባት። ጌጧን ለባዳ ማሳየት የለባትም። ውበቷን የሚያሳይ አለባበስ መከተል የለባትም። ከወንዶች ጋር የሚኖር ቅልቅልን (ኢኽቲላጥን) መጠንቀቅ አለባት።

በሱዳን ዩኒቨርሲቲ የሸሪዓ መምህር የሆኑት ዶክተር ዐብዱል-ሐይ ዩሱፍ እንዲህ ይላሉ፡-

አንድን ነገር ለመፍቀድ (ተህሊል)፣ ለመከልከል (ተህሪም)፣ ግዴታ ለማድረግ (ውጁብ)፣ በተወዳጅነት (መንዱብ) ለመፈረጅ የሚመጡ የሸሪዓ መልእክቶች በሙሉ ሁለቱን ፆታ እንደሚመለከት የታመነ ነው። ይኸውም በወንዶች ወይም በሴቶች ላይ የሚገድብ መረጃ እስካልመጣ ድረስ ነው። በሴቶች ወይም በወንዶች ላይ የሚገድብ መረጃ ሲመጣ ግን ልቅ የነበረው የሸሪዓ መልእክት በመጣው ገደብ ይታጠራል። ይህ ከታወቀ ተከታዩን ነጥብ ማብራራት እንችላለን፡፡

አንደኛ፡- ሸሪዓው አካልን ብቁ ማድረግ እና ጤናን መጠበቅ ተፈላጊ እንደሆነ አስገንዝቧል። ይህም ጥቅል በሆኑ የሸሪዓው መልእክቶች ውስጥ ሰፍሯል። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ይላሉ፡-

المؤمن القوي خير وأحبّ إلى الله من المؤمن الضعيف وفي كلّ خير

“ጠንካራ ሙእሚን ከደካማ ሙእሚን የተሻለ እና አላህ ዘንድ የተወደደ ነው። ሁለቱም ውስጥ ግን መልካም ነገር አለ።”

ዑመር ኢብኑል-ኸጧብም እንዲህ ይላሉ፡-

علموا أولادكم السباحة والرماية وركوب الخيل

“ልጆቻችሁን ውሃ ዋና፣ ቀስት ውርወራና ፈረስ ግልቢያ አስተምሯቸው።”

አስለም ከሚሰኘው ጎሳ የሆኑ ሰዎች ቀስት ውርወራ ሲጫወቱ  የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) አገኟቸው። ከዚያም እንዲህ አሉ፡-

ارموا بني إسماعيل فإن أباكم كان راميا

“ወርውሩ ኢስማዒል ልጆች፤ አባታችሁ ቀስት ወርዋሪ ነበር።”

በሌላ ሐዲስም የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ አሉ፡-

من تعلّم الرمي ثم تركه فليس منّا

“ቀስት ውርወራ የተማረ ከዚያም የረሳው ሰው ከእኛ አይደለም።”

ሁለተኛ፡- በነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ድርጊት እንደተረጋገጠው ነብያችን (ሰ.ዐ.ወ) አካልን ብቁና ጠንካራ የሚያደርጉ እና ለጂሃድ የሚያዘጋጁ ነገሮችን በሙሉ ያበረታቱ ነበር። ጉልበታቸውን በሚያጠናክር ሁኔታ አካላቸው የታነፁ ፈረሶችን እና ያልታነፁ ፈረሶችን አወዳድረዋል። ከዓኢሻ  ጋር ተወዳድረዋል። አንዴ ቀደመቻቸው፤ ሁለተኛው ውድድራቸው ላይ ደግሞ እርሳቸው ቀደሟት። ከዚያም እንደጨዋታ “هذه بتلكይህኛው በዛኛው ይካካሳል።” አሉ። ሐሰን እና ሑሰይን በርሳቸው ፊት ትግል ተወዳድረዋል። “ይህ ነው ሐሰን!” ይሉም ነበር።

ሦስተኛ፡- በዚህ ጉዳይ ላይ ያሉትን ሸሪዓዊ መርሆች መዘንጋት አይገባም። ጥቅሙን ማግኘት እንደምንፈልገው ሁላ ጉዳቱንም ማስወገድ እና ራሳችንን አላህን ከማመፅ መጠበቅ አለብን። ይህን በተከታዮቹ ነጥቦች መግለፅ ይቻላል፡-

  1. ስፖርት ወደ አንዳች ግብ የሚያደርስ መንገድ እንጂ ዋና ዓላማ አይደለም። ስለዚህ በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች መሰረት ወዳጅና ጠላት መኳኳን የለም። እንደውም ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ለጠላትነት እና ለመቃቃር መንገድ የቀደደ እንደሆነ ወደ ሐራምነት ይለወጣል። ይህ ችግር በእግር ኳስ ጨዋታ አፍቃሪዎች ላይ ይስተዋላል። ከሚደግፉት ቡድን ጥቅም አኳያ ይዋደዳሉ፤ ይጣላሉ። አንዳንዴ ደም አፋሳሽ የሆኑ ጦርነቶች ይካሄዳሉ።
  2. ስፖርት በልኩ መሆን አለበት። እድሜን ለርሱ መለገስ ጊዜን በሙሉ- በሌሎች ኃላፊነቶች ሂሳብ- ለርሱ መስጠት አይቻልም። በዚህ ጎን ስፖርት እንደሌሎች የሚፈቀዱ ነገሮች (ሙባሃት) ይታያል። የሚፈቀዱ ነገሮች ላይ ወሰን ማለፍና ድንበር መጣስ እርምና የተጠላ ነው። ሁሉም ነገር በልኩ መሆን አለበት።
  3. ለመዝናናት የሚከወኑ- እግር ኳስ እና ቅርጫት ኳስን የመሳሰሉ- ስፖርቶች እና ለጂሃድ የሚያገለግሉ- የአካል ብቃት እና ቀስት ውርወራን የመሰሉ- ስፖርቶች የተለያየ ብይን ነው ያላቸው። የመጀመሪያዎቹ ይፈቀዳሉ። ሁለተኞቹ ደግሞ ዋጂብ ወይም ተወዳጅ ይሆናሉ። ሁሉንም አጅር የሚያስገኙ- የፊሰቢሊላህ ናቸው- ማለት አይቻልም።
  4. በእነዚህ ሁሉ ብይኖች ውስጥ- ስፖርቶቹ- ከሌሎች እርም ነገሮች ያገለሉ መሆን አለባቸው። መሰዳደብ፣ ፍስቀት፣ ሃፍረተ ገላን መግለጥ፣ ወንድና ሴት መቀላቀል፣ ሶላትን ማሳለፍ፣ ሰዎችን ማስከፋት… ስፖርት ውስጥ እርም ነው፤ በሌላ ጊዜም እርም እንደሆነው ሁሉ ማለት ነው። ወደሞት የሚያደርስ፣ ህይወትን አደጋ ላይ የሚጥሉና ክፉ ውጤት ያላቸውን ስፖርቶችም መራቅ ያስፈልጋል። ውሃ ዋና እና እግር ኳስ ላይ እንደተለመደው ደግሞ ሃፍረተ ገላን ማሳየት አይቻልም። “ታፋ ዓውረት (ሃፍረተ ገላ) ነው።” ይላሉ ታላቁ ነብይ።
  5. ወንድ የራሱ መለዮ አለው፤ ሴትም እንደዚሁ ተፈጥኣዊ መለያ አላት። ሴት ከሴትነት ተፈጥሮዋ የሚያወጣትን ስፖርት መስራት የለባትም። ለምሳሌ የአካል ግንባታ (የቅርፅ ውድድር) ሴትን ከተፈጥሮኣዊው ማንነቷ ያወጣታል። ምክንያቱም ታላቁ ነብይ አንዲት ሴት እንደወንድ ስትራመድ አይተዋት “እርጉም ናት!” ብለዋል።

ወላሁ አዕለም!