ሴት የሐጅ ስራዎችን እንዲከውንላት ሌላን ሰው መወከል ትችላለች?

Home የፈትዋ ገጽ ሐጅና ዑምራ ሴት የሐጅ ስራዎችን እንዲከውንላት ሌላን ሰው መወከል ትችላለች?

ጥያቄ፡- በዚህ አመት- አላህ ካለ- እናቴን ይዤ ሐጅ አደርጋለሁ። እናቴ እድሜዋ ትልቅ ነው። አርጅታለች። ህመምተኛና ደካማ ሴት ናት። ስለዚህ እናቴን ተክቼ መስራት የምችላቸው የሐጅ ስራዎች የትኞቹ ናቸው?


መልስ፡- ጠጠር መወርወር እና እርድ ማከናወን ላይ እናትህን መተካት ትችላለህ። ከዚህ ውጪ ያሉት የሐጅ ስራዎች ላይ ግን እናትህ በራሳቸው መፈጸም አለባቸው እንጂ ልትወከላቸው አትችልም። ክብርት እናትህ በመኪና ተሳፍረው ወደ ሚናና ዐረፋ መሄድ ይችላሉ። እዚያ በሚቆዩበት ጊዜም ወንበር ላይ ሊቀመጡ ወይም እረፍት ሊያደርጉ ይችላሉ። ጠዋፍን በሸክም ሊከውኑት ይችላሉ። ወይም ተንቀሳቃሽ ወንበር ሊገለገሉ ይችላሉ። በነዚህ ስራዎች ላይ በሙሉ ልታግዛቸው ትችላለህ። አጅርም አለህ!

በቁድስ ዩኒቨርሲቲ የፊቅህና ኡሱሉል-ፊቅህ መምህር የሆኑት ዶክተር ሑሳሙዲን ቢን ሙሳ ዒፋና እንዲህ ይላሉ፡-

“በመሰረቱ ሐጀኛ የሐጅ ስራዎችን በሙሉ በራሱ መከወን ነው ያለበት። ዑለሞች ጠጠር መወርወር እና በእርድ ተግባር ላይ ሰውን መወከል እንደሚቻል ገልፀዋል። ጠጠር መወርወር ላይ መወከል የሚቻለው ሸሪዓዊ ምክንያት ወይም ችግር- ሕመም፣ እርግዝና፣ እርጅና…- በሚኖርበት ጊዜ ነው። በተጨማሪም ከፍተኛ ግፊያ በመኖሩ ምክንያት ሴትየዋ ለነፍሷ የፈራች እንደሆነ ጠጠር የሚወረውርላት ሰው መወከል ትችላለች። ተወካዩ ደግሞ መጀመሪያ ለራሱ ከወረወረ በኋላ ነው ውክልና ለሰጠው አካል መወርወር ያለበት።

እርድን ግን ምንም ዓይነት ችግር የሌለበትም ሰው በውክልና እንዲያሳርድ ይፈቀድለታል። ነገርግን የተሻለው ሰውየው ራሱ ቢያርድ ነው። ይህም የአላህ መልእክተኛ ሱና ነው። ሐዲስ ላይ እንደተረጋገጠው፡- “የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ስድሳ ሦስት ግመሎችን አርደዋል። ከዚያም የቀሩትን ግመሎቻቸውን እንዲያርዱ ዓሊይን ወክለዋል።” ሙስሊም ዘግበውታል።

የቀሩት የሐጅ ስራዎች ላይ ውክልና አይፈቀድም። ጠዋፍ፣ በሶፋና በመርዋ መሀል መመላለስ (ሰዕይ)፣ ዐረፋ ላይ መገኘት፣ ሙዝደሊፋና ሚና ላይ ማደርን የመሳሰሉ የሐጅ ማዕዘናትና ግዴታዎች ሐጀኛው በራሱ ሊፈፅማቸው የሚገቡ ናቸው። ህመምተኛ ከሆነ ጠዋፍና ሰዕይ ላይ ሰው ተሸክሞት ቢፈፅም ችግር የለውም። ወደ ዐረፋና ወደ ሚና ሲሄድም በመኪና ቢጫን ችግር የለውም። ዐረፋ ላይ ተቀምጦ ማሳለፍ ለጤነኛውም ሆነ ለህመምተኛው የተፈቀደ ነው።

በጥቅሉ ወላጅ እናትህ ጠጠር መወርወር እና እርድ ላይ ብቻ ሰው መወከል ይችላሉ። ከዚህ ውጪ ያሉ የሐጅ ሥራዎች ላይ ግን በራሳቸው ሊፈፅሙ ይገባል። አንተም ልትረዳቸው ይገባል። ወይም ጠዋፍና ሰዕይ የሚያስደርጋቸው ሰው ልትቀጥርላቸው ይገባል።”

አላሁ አዕለም!