ሱና ሶላቶች ላይ የኒያዎች መዋሃድ አለ?

Home የፈትዋ ገጽ ሰላት ሱና ሶላቶች ላይ የኒያዎች መዋሃድ አለ?

ጥያቄ፡- እንደ ተሒየቱል-መስጂድ ያሉ ሱና ሶላቶችን በአዛንና በኢቃም መካከል ካሉት ሶላቶች ጋር አጣምሮ መስገድ ይቻላል?


መልስ፡- የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) መስጂድ የገባ ሰው ከመቀመጡ በፊት ተሒየቱል-መስጂድ እንዲሰግድ አነሳስተዋል። እንዲህ ይላሉ፡-

إِذَا دَخَلَ أَحَدُكُمُ الْمَسْجِدَ فَلْيَرْكَعْ رَكْعَتَيْنِ قَبْلَ أَنْ يَجْلِسَ (متفق عليه واللفظ للبخاري)

“እያንዳንዳችሁ መስጂድ ከገባችሁ ከመቀመጣችሁ በፊት ሁለት ረከዐ ስገዱ።” ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል። አገላለፁ የቡኻሪይ ነው።

ሰውየው ተሒየቱል-መስጂድንና በአዛን እና በኢቃም መካከል ያሉትን ሱናዎች አደባልቆ መስገድ ይችላል። ይህን ሻፊዒዮቹ እና ሌሎችም በግልፅ አስቀምጠዋል። ኢማም አስ-ሲዩጢይ “አል-አሽባህ ወን-ነዟኢር” የተሰኘው መፅሀፋቸው ላይ እንዲህ ይላሉ፡- “ሰውየው ፈርድ ሶላትን እና ተሒየቱል-መስጂድን ነይቶ ሶላት ቢጀምር ሶላቱ ይሆንለታል። ሁለቱም ሶላቶች ይገኙለታልም። ‘ይህ ባልደረቦቻችን የተስማሙበት ነው። ብዙ አመታት ካጠናሁት በኋላ በሁሉም ዑለሞች ዘንድ ልዩነት አላገኘሁም።’ ይላሉ ነወዊይ፤ ሸርሑል-ሙሀዘብ ላይ።”

ይኸው መፅሀፍ ሌላ ስፍራ ላይ ተሒየቱል-መስጂድና ሌላ ሶላትን አጣምሮ ስለመስገድ ሲዩጢይ እንዲህ ይላሉ፡- “ሰውየው ባይነይታትም በውስጡ መገኘቷ አይቀርም።”

ተሒየቱል-መስጂድ ያስፈለገበት ምክንያት- ምንም አይነት ሶላት ይሁን- ሶለት ሳይሰግዱ መስጂድ አለመቀመጥ ብቻ ነው። ትኩስ ሶላትም ይሁን ቀዷእ፣ ከፈርድ ሶላት ጋር የተያያዙ መደበኛ ሱዎችም ይሁኑ ስድ ሱናዎች ወይም በሰበብ ወይም በወቅት የተገደቡ ሱናዎች… ልዩነት የለውም። መስጂድ እንደገባ ሰውየው ከነዚህ ዓይነት ሶላቶች አንዱን ከሰገደ ተሒየቱል መስጂድን በውስጡ ያገኛል።

ወሏሁ አዕለም!