ሰይጣን አሳስቶኝ ነፍሴን በደልኩ…ከወንጀሌ እንዴት ልጽዳ?

Home የፈትዋ ገጽ ማህበራዊ ጉዳዮች አኽላቅና አዳብ ሰይጣን አሳስቶኝ ነፍሴን በደልኩ…ከወንጀሌ እንዴት ልጽዳ?

ጥያቄ፡- እድገቴና ቤተሰቤ በመልካም የዲን መንገድ ላይ ቢሆንም ሰይጣን አሳስቶኝ ነፍሴን በደልኩ። በአንድ አጋጣሚ ላይ ለእረፍትና ለመዝናናት ከትምህርት ቤት ጓደኞቼ ጋር ከአዲስ አበባ እርቀን ወደ ሶደሬ ሄደን ነበር። እናም በዚሁ አጋጣሚ በጓደኞቼ ግፊት እርኩሱን ኸምር (አልኮል) ጠጣሁ። ዝሙትም ፈጸምኩ። አሁን ግን ሆኜ ሳስብ ለአንድ ቀን ከንቱ ይሉኝታና እርካታ የፈፀምኩት ወንጀል እንደ እግር እሳት ይለበልበኛል። ኸምር የጠጣና ዚና የፈጸመ ሰው ሸሪዓዊ ቅጣት በኔ ላይ ባለመፈፀሙም ልቤ ሊረጋጋ አልቻለም። ከኃጢያቴ እንድጠራ ምን ማድረግ እንዳለብኝ ግራ ገባኝ። ጨነቀኝ። እንቅልፍ ከተኛው ቆየሁ። እባካችሁን መፍትሄ እሻለሁ!


መልስ፡- እኛ የምንልህ አላህ (ሱ.ወ) ይህንን ንጹህ መንፈስ ስላደለህ አመስግን። የኃጢያትህን እድፍ ለማበስ ይኸው ይበቃኻል- ኢንሻአላህ። ከአሁን በኋላ ተመሳሳይ ወንጀል ላለመፈፀም ተጠንቀቅ። መጥፎ ጓደኞችን ራቅ። ከመስጂድ አትጥፋ። በጎ ሥራዎችን አብዛ። ኢስቲግፋር ከምላስህ አይለይ። ወንጀልህን ለሰዎች አትንገር። ባንተና በጌታህ መሀል ማልቀስህን አታቋርጥ። ወንጀልህን አትርሳ። የአላህን ምህረትና እዝነትም አትዘንጋ። እንዲህ ከሆንክ አላህ (ሱ.ወ) ይምርሃል። ባለንበት ሀገራዊ ተጨባጭ የጠቀስካቸውን ሸሪአዊ ቅጣቶች (ሃድ) መፈፀም አግባብ አይደለም። ስለዚህ የጠቀስንልህ መፍትሄዎች ብቻ በቂ ናቸው። አላህ የተሻለ ያውቃል!