መእሙም (ተከታይ) ሆኖ ፋቲሓን መቅራት

Home የፈትዋ ገጽ ሰላት መእሙም (ተከታይ) ሆኖ ፋቲሓን መቅራት

ጥያቄ፡- መእሙም ፋቲሓን ይቀራል?


መልስ፡- ቢስሚላሂር-ረሕማኒር-ረሒም አልሐምዱሊላሂ ረብ-ቢል-ዓለሚን ወስ-ሶላት ወስ-ሰላም ዐላ ረሱሊል-ላህ

የፊቅህ ልሂቃን በዚህ ጉዳይ ላይ አራት ዓይነት ሃሳቦችን አንጸባርቀዋል፡-

አንደኛው፡- ሐነፊዮች ዘንድ ድምጽ ከፍ ተደርጎም ሆነ ዝቅ ተደርጎ በሚሰገዱ ሶላቶች ላይ ተከታይ የሆነ ሰው ፋቲሐን ማንበቡ በጥብቅ የተጠላ ነው፡፡ ምክንያቱም በሐዲስ እንደተዘገበው የአላህ መልክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡-

من كان له إمام فقراءة الإمام له قراءة

“ኢማምን ተከትሎ እየሰገደ ያለ ሰው የኢማሙ ንባብ ለርሱም ነው፡፡”

ከኢማም ጋር ተከትሎ የሚሰገድን ሰው ቁርኣን ከማንበብ መከልከሉ “ከሰማንያ ታላላቅ ሶሐቦች ተገኝቷል፡፡”

ሀለተኛው፡- ሻፊዒዮች በበኩላቸው መእሙም ፋቲሐን ማንበብ ግዴታው ነው የሚል እምነት አላቸው፡፡ ምክንያቱም የአላህ መልክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) እንዲህ ብለዋል፡-

لا صلاة لمن لم يقرأبفاتحة الكتاب

“ፋቲሐን ያላነበበ ሰው ሶላት የለውም፡፡”

ድምጽን ዝቅ አድርጎ በሚሰገዱት የሶላት ስፍራዎች ላይ ደግሞ ከፋቲሐ በተጨማሪ ሌሎች ሱራዎችን ማንበብም ሱና ነው፡፡ ድምጽ ከፍ በሚልባቸው የሶላት ሁኔታዎች ላይ ግን ከፋቲሐ ውጪ ሌሎች ሱራዎችን ማንበብ የተጠላ ነው፡፡

ሦስተኛው፡- የማሊኪዮች አቋም ነው፡፡ ድምጽ ዝቅ በሚደረግበት ሁኔታ ላይ ቁርኣን ማንበብ ይወደዳል፡፡ ድምጽ ከፍ በሚልበት ሁኔታ ላይ ቁርኣንን ማንበብ የተጠላ ነው፡፡ ይህ አቋም የመነጨው ሁለቱን ተቃራኒ መልዕክት ያላቸው የሚመስሉትን ዘገባዎች በአንድ ላይ በማድረግ ነው፡፡

አራተኛው፡- ሐንበሊዮች ድምጽ ዝቅ በሚልባቸው የሶላት ሁኔታዎች ላይና ድምጽ ከፍ ተደርጎ ቁርኣን በሚነበብባቸው የሶላት ሁኔታዎች ላይ ደግሞ ኢማሙ ዝም የሚልባቸውን አጋጣሚዎች በመጠቀም ቁርኣን ማንበብ ይወደዳል፡፡ ይህም አቋም በጉዳዩ ላይ የተገኙትን ሁለቱን ዘገባዎች በአንድ ላይ በማጣመር የተገኘ ነው፡፡

በእኛ አመለካከት -የተሻለ የሚመስለን- የሐንበሊዮቹ ሃሳብ ነው፡፡ ምክንያቱም በርዕሰ-ጉዳዩ ላይ የተገኙትን ሁለቱን ዘገባዎች በተሻለ ሁኔታ በማጣመር የተገኘ ውሳኔ የነርሱ ነው፡፡ በመሆኑም የኢማሙን ሁኔታ በመመልከት ክፍተቶችን በቁርኣን ንባብ መዝጋት የተሻለ ነው፡፡ ኢማሙ ፋቲሐን ለማስነበብ የሚያስችል ምንም ክፍተት የማይሰጥ ከሆነ መእሙሙ ፋቲሐን የማንበብ ግዳጅ የለበትም፡፡ ይልቁንስ የኢማሙን ንባብ በጥሞና ያዳምጥ፡፡ ነገርግን ኢማሙ ክፍተት የሚሰጥ ከሆነ በክፍተቱ ላይ ተከታዩ አጋጣሚዎቹን ተጠቅሞ ፋቲሓን ብቻ ያነባል፡፡ ይህ በነዚህ አጋጣሚዎች ነፍስ ከሶላት ርቃ በሃሳብ እንዳትጓዝ መሰብሰቢያ ይሆናል፡፡ ድምጽ ዝቅ ተደርጎ በሚሰገድባቸው ሁኔታዎች ላይ ግን መእሙም ነፍሱን በቁርኣን መጥመድ ይገባዋል፡፡

አላህ የበለጠ ያውቃል!