ጥያቄ፡- መስጂዶችን በሰዎች ስም መሰየም ወይም በገነባቸው ሰው ስም መሰየም በሸሪዓው የሚከለክል ነገር አለበት?
መልስ፡- ቢስሚላሂር-ረሕማኒር-ረሒም አል-ሐምዱሊል-ላሂ ረብ-ቢል ዓለሚን ወስ-ሶላት ወስ-ሰላም ዐላ ረሱሊላህ
መስጂዶችን በሰዎች ስም መሰየም ችግር የለውም። በገነባው ሰው ስም ወይም የዐሊም፣ የመሪ፣ የደግ ሰው ወይም የጀግኖችን ስም ለማስታወስ በሰዎች ስም መሰየም ክልክል አይደለም። ወይም ከሌሎች መስጂዶች ለመለየት እና በቀላሉ ለመግባባት ሲባል በሰዎች ስም መሰየምም ችግር የለውም። ለምሳሌ፡- “ዐምር ቢን አል-ዐሲ” መስጂድ፣ “አቡደርዳእ” መስጂድ፣ “አቡ ዑበይዳ” መስጂድ፣ “ዐኢሻ” መስጂድ፣ “ኢማም ሐሰን” መስጂድ ወ.ዘ.ተ. እየተባሉ የሚጠሩ መስጂዶች በየሀገሩ እና በየከተማው ይገኛሉ። ስለዚህ ስሙን ያወጡት ሰዎች ኒያቸው መልካም እስከሆነ ድረስ የሚከለክል ነገር የለም። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) እንዲህ ይላሉ፡-
إنما الأعمال بالنيات
“ሥራዎች ሁሉ በኒያ (በዓላማቸው) ይመዘናሉ።”
ነገርግን ለመስጂዱ ስም የሚያወጡት ለመፎከር እና ለታይታ ከሆነ ግን ክልክል ነው።
አላሁ አዕለም!