ሒጃብ የማትለብስ ሴት ሶላትና ጾም ቀቡል ይሆናል?

Home የፈትዋ ገጽ ቤተሰብ ሒጃብ የማትለብስ ሴት ሶላትና ጾም ቀቡል ይሆናል?

ጥያቄ፡- ሒጃብ ለባሽ አይደለሁም። አላህ ይቅር እንዲለኝና ሒጃብን እንዲያገራልኝ ዱዓ አድርጉልኝ። አሁን መጠየቅ የፈለኩት ሶላቴንና ጾሜን አላህ ይቀበለኝ ይሆን?


መልስ፡- ለተመሳሳይ ጥያቄ የግብፁ ዳሩል-ኢፍታእ የሚከተለውን መልስ አስፍሯል፡-

የሙስሊም ሴት የአለባበስ ስርዐት አላህ የደነገገው ግዴታ ነው።  አላህ እንድትሸፍነው ያዘዛትን አካሏን ከባዳ ወንዶች መሸፈን አለባት።  ሸሪዐው የደነገገው የሴት አለባበስ – ከፊትና ከእጅ ውጪ- መላ አካሏን የሚሸፍን ልብስ ነው። ቅርፅና የቆዳ ቀለምን የሚያሳይ ልብስም መሆን የለበትም።

ሸሪዐዊ ግዴታዎች አንዱ ሌላውን አይተካም። ለምሳሌ ሶላት የሰገደ ሰው ሶላት መስገዱ ጾምን ከመጾም አይተካለትም። የሰገደችና የጾመችም ሸሪዐው ያዘዛትን አለባበስ ለመተው ሰበብ አይሆናትም። …

የምትሰግድ እና የምትጾም ነገርግን አላህ ያዘዛትን ሒጃብ የተወች ሙስሊም ሴት በሶላቷና በጾሟ ምንዳን ልታገኝ እንደመቻሏ ሁሉ የታዘዘችውን ሒጃብ በመተወዋ ደግሞ ልትቀጣ ትችላለች። መስገድና መጾሙ ከኃጢያተኝነት አያድናትም። ሶላትን እና ሌሎች አምልኮዋችን የመቀበልና ያለመቀበል ጉዳይ የአላህ ነው። ስለዚህ ኃጢያተኛ ቢሆንም- ሙስሊም ግለሰብ- በአላህ ላይ ያለውን ጥርጣሬ ማሳመር አለበት። የአላህ እዝነት ሆኖ- በጎ ተግባር- ኃጢያትን ያብሳል። በጎ ስራን ግን ኃጢያት አይሰርዘውም። ኃጢያተኛ ጌታው ዘንድ ያለውን መዝገብ በተውበት ማፅዳትና አዲስ የህይወት ምዕራፍ ለመጀመር መጣር አለበት። እህታችን ሆይ ነገ ዛሬ ሳትይ ዛሬውኑ ወደ መሀሪው ጌታሽ እንድትመለሽ አዳራ እንልሻለን። ራስሽን የምህረት ቦታው ላይ ለማስገኘትም ጥረት ማድረግ እንዳለብሽ እናሳስብሻለን።

ሒጃብ ማለት ሙስሊም ሴት አላህ የሰጣትን ውበት የምታመሰግንበት አምልኮዋ ነው። ውበት በማይገባው ቦታ አይገለጥም። የአላህ ፀጋ ነውና ፀጋውን ደግሞ እርሱ የማይወደው ስፍራ ላይ ማዋል ስጦታውን መካድ ነው!…

አላህ አንቺንም እኛንም ይማረን። የሰራነውን በጎ ስራም ይቀበለን።

አላህ የተሻለ ያውቃል!