ሐጅ ላይ ያለ ሰው በምን አይነት ስራ ይጠመድ?

Home የፈትዋ ገጽ ሐጅና ዑምራ ሐጅ ላይ ያለ ሰው በምን አይነት ስራ ይጠመድ?

ጥያቄ፡- በሐጅ ጊዜ ውስጥ ሐጀኛ ሊፈፅማቸው የሚገቡ ስራዎች ምንድን ናቸው?


መልስ፡- ታላቁ ዐሊም ዶክተር ዩሱፍ አል-ቀረዳዊ (አላህ ይጠብቃቸውና) እንዲህ ይላሉ፡-

“ሐጀኛ በሐጅ ጊዜው አላህን በማውሳት-በዚክር-፣ በዒባዳ፣ የአላህን ትዕዛዛት በመከወን እና ወደ አላህ የሚያቃርቡ በሆኑ በጎ ሥራዎች-በሶደቃ፣ ደካሞችን በማገዝ፣ እውቀት የሌላቸውን በማስተማር…- ራሱን መጥመድ ነው ያለበት። ባገኘው አጋጣሚ አብዝቶ ቁርኣንን ማንበብ ይወደድለታል። በቻለው አቅም ታላቁ መስጂድ (መስጂዱል-ሐረም) ውስጥ ኢዕቲካፍ ማድረግ ተወዳጅ ስራው ነው። ካልተቸገረ ወይም ሰዎችን ማጣበብ እስካልሆነበት ድረስ በአላህ ቤት ላይ መዞር (ጠዋፍ ማድረግ) እጅግ ተመራጭ ስራ ነው። ጠዋፍ አንድ ሙስሊም መካ ውስጥ እንጂ ሊያገኘው የማይችለው አምልኮ ነው። ጠዋፍ የዑምራ ግማሽ ነው። ዑምራ ጠዋፍና በሶፋና በመርዋ መካከል መመላለስ ነው።

ሐጀኛ አላህ እርም ካደረገበት ነገር ዐይኑን መስበር አለበት። ምላሱንም ከሃሜት፣ ከስድብና ከቧልት ማቀብ አለበት። እጁንም ሰዎችን ከማስቸገር እና ከማስከፋት መጠበቅ አለበት። ሙስሊም ማለት ሙስሊሞች ከምላሱና ከእጁ ተንኮል የዳኑለት ሰው ነው። አላህ በሐጅ ውስጥ የወሲብ ወሬን፣ ፍስቀትን እና ክርክርን እርም አድርጓል። ይህ ጉዞ የሰላምና የፍቅር እንዲሆን የክርክር እና የጥላቻ መንገዶችን አላህ ዘግቷል።”

ወላሁ አዕለም!