ሐጅ ላይ ሁለት ኒያዎችን መሰብሰብ

Home የፈትዋ ገጽ ሐጅና ዑምራ ሐጅ ላይ ሁለት ኒያዎችን መሰብሰብ

ጥያቄ፡- አንድ ሰው ጾም ሱና የሆነበትን ቀን ከአንድ በላይ በሆነ ኒያ ከጾመው ምንዳው በኒያው ልክ እንደሆነ አውቃለሁ። ምክንያቱም የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) “ኢነመል አዕማሉ ቢኒያ” (ስራ ሁሉ የሚለካው በኒያ ነው) ብለዋል። ጥያቄዬ ምንድን ነው፡- ሰውየው ግዴታ የሆነበትን ሐጅ በሑለት ኒያዎች መፈፀም ይችላል? ለምሳሌ አንዲትን ሐጅ ለራሱ እና ለአንድ ወላጁ ሊነይትባት ይችላል? አላህ ይስጥልኝ!


መልስ፡- የአንድ ሰው ጫንቃ- በሐጅ ተጨባጭ- ከአንድ ኒያ በላይ ሊሸከም አይችልም። ሰውየው ለነፍሱ ሐጅ ማድረግን ከነየተ ለነፍሱ ብቻ ነው የሚሆንለት። ለወላጆቹ ካደረገው ደግሞ ለአንድ ወላጁ ነው የሚሆነው። እርሱ ግን ለወላጅ በጎ የመዋልን ምንዳ ያገኛል። ስለዚህ ሐጅን ለአንድ ሰው እንጂ ለብዙ ሰዎች ማድረግ አይቻልም። አንድ ሰው አንድ ሐጅን ለነፍሱም ለወላጆቹም ሊያደርግ አይችልም። ሐጅ ለሰዎች የማይጋራ አምልኮ ነው።

የንጉሳዊቷ ሳዑዲት ዓረቢያ ሙፍቲ የነበሩት ሸይኽ ዐብዱል-ዐዚዝ ቢን ባዝ (ረሒመሁሏህ) እንዲህ ይላሉ፡-

“ሐጅ በአመት አንድ ጊዜ የሚከወን አምልኮ ነው። ስለዚህ ሰውየው ሐጁን ለነፍሱ ከነየተው ለነፍሱ ብቻ ነው የሚሆነው። ለአባቱ ካለውም ለአባቱ ነው የሚሆነው። ለአባቱ በጎ በመዋሉ ምንዳውን አያጣም። ዑምራም እንዲሁ ነው። ለሞተው፣ ላረጀው ወይም ለታመመው አባቱ ወይም ለእናቱ ዑምራ ያደረገ ሰው የበጎ ውለታውን ምንዳ አያጣም።

ነገርግን ለሁለት ወላጆች በአንድነት ዑምራ ወይም ሐጅን መነየት አይቻልም። ምክንያቱም ሐጅ እና ዑምራ ለአንድ ሰው ብቻ የሚደረጉ መጋራትን የማይቀበሉ አምልኮዎች ናቸው። ስለዚህ ኒያውን ለአባቱ ካደረገው ለአባቱ ነው የሚሆነው። ለእናቱ ካደረገው ለእናቱ ብቻ ነው የሚሆነው። እርሱ የሚያገኘው ምንዳ ለወላጆች በጎ የመዋልን ምንዳ ነው የሚሆነው። ለሁለቱ በአንድነት ኒያ ቢያደርግ ወይም ለአባቱና ለነፍሱ ቢያደርግ ወይም ለእናቱና ለራሱ ቢያደርግ በሁሉም ሁኔታዎች ለርሱ ብቻ ነው የሚሆነው።”

አላሁ አዕለም!