ሀጃጆች ኢሕራም የሚያደርጉበት ቦታ

Home የፈትዋ ገጽ ሐጅና ዑምራ ሀጃጆች ኢሕራም የሚያደርጉበት ቦታ

ጥያቄ፡- መካ ወይም መዲና ውስጥ ለሐጅ የተወሰነ የኢሕራም ቦታ አለ? ካለ የት ነው?


መልስ፡- ሐጅ ወይም ዑምራ ማድረግ የሚሻ ሰው ኢሕራም የሚያደርግበት ቦታን አስመልክቶ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) የገደቡት ቦታ አለ። ሐጅ ወይም ዑምራ ማድረግ የሚፈልግ ሰው ሊያልፋቸው የማይገቡ የኢሕራም ስፍራዎችን (ሚቃትን) ወስነው ገልፀዋል። ሰውየው እነዚህን ስፍራዎች ከማለፉ በፊት ኢሕራም ማድረግ እንዳለበትም አሳውቀዋል። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ለመዲና ሰዎች ዙል-ሑለይፋ የተሰኘውን ስፍራ መድበዋል። ይህ ስፍራ ከመካ 450 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ያለ ስፍራ ነው። ለሻም፣ ለምዕራብ ዐረቢያ እና ለግብፅ ሰዎችም አል-ጁሕፋ የተሰኘ ስፍራን መድበዋል። ራቢግ ከሚባለው መንደር 187 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ያለ ስፍራ ነው። ለሒጃዝ (የአሁኗ ሳዑዲያ) ደጋው ክፍል ቀርኑል-መናዚል የተሰኘውን ስፍራ መድበዋል። ይህ ቦታ ከመካ 95 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ስፍራ ነው።

ለየመን ሰዎች (ለቆለኞቹ) የለምለም የተባለውን ስፍራ መድበዋል። ይህ ቦታ ከመካ 95 ኪሎሜትር ርቆ የሚገኝ ነው። ለዒራቅ ሰዎች ዛቱ ዒርቅ የተሰኘውን ስፍራ መድበዋል። ይህም እንዲሁ ከመካ በ95 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ነው። ከዚያም የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡-

هن لهن ولمن أتى عليهن من غير أهلهن ممن أراد الحج أو العمرة ومن كان دون ذلك فمن حيث أنشأ حتى أهل مكة من مكة

“እነዚህ ስፍራዎች ለአካባቢው ሰዎችና በነርሱ በኩል ለሚያልፉ- ሐጅና ዑምራ ለማድረግ ለሚሹ- ከአካባቢው ነዋሪዎች ውጪ ለሆኑት ሰዎች ናቸው።  የመነሻ ቦታቸው ከነዚህ ክልሎች ወደ መካ የቀረበ የሆነ ሰው ከተነሳበት ኢሕራም ያድርግ። የመካ ሰዎች ራሳቸው ከመካ ኢሕራም ያድርጉ።”

ስለዚህ ከመዲና ተነስቶ ሐጅ ወይም ዑምራን ኢሕራም የሚያደርግ ሰው ዚል-ሑለይፋ የተሰኘው ስፍራ ላይ ኢሕራም ያድርግ። ከመካ ሐጅ ማድረግ የፈለገ ሰው- ከራሷ- ከመካ ኢሕራም ያድርግ። ከሌሎች ስፍራዎች የሚመጣ ሰውም ልክ የአላህ መልእክተኛ በገለፁት መልኩ ኢሕራሙን ያከናውናል።

አላህ የተሻለ ያውቃል!