ልጆችን በሷሊሖች ስም መጥራት ምን ጥቅም ያስገኛል?

Home የፈትዋ ገጽ ቤተሰብ ልጆችን በሷሊሖች ስም መጥራት ምን ጥቅም ያስገኛል?

ጥያቄ፡- …ከዘመዶቼ ጋር ተሰብስበን እየተጨዋወትን እያለን አዲስ ለተወለደው ልጄ ሥም ስለማውጣት መወያየት ጀመርን። በዚህ መሀል በአንቢያዎች ወይም በሶሐቦች ስም በመጠራት ዙርያ ክርክር ጀመርን። አንዷ ሙሐመድ ወይም ዘከሪያ የሚባሉ ስሞችን እንደማትወድ ተናገረች! “ያረጁ ሥሞች ናቸው” ስትል ምክንያቷንም አስረዳች። የአላህን መልእክተኛ- ሙሐመድን (ሰ.ዐ.ወ)- እንደምትወድና እንደምታፈቅር ግን አስረግጣ ተናገረች። ሥሙ ግን ዘመናዊ አይደለም። ስለዚህ ዘመናዊ ሥም እመርጣለሁ አለች። ልክ እንዲሁ ዓኢሻ፣ ኑሰይባ፣ ዒሳ፣ ፋጢማ… የሚሰኙ ስሞችም ደስ እንደማይላት ተናገረች። ዘመናዊ ሥሞች ብላ የጠቀሰቻቸው ደግሞ ሸረፍ፣ ታሚር… የሚሰኙትን እንደሆነም አስረዳች። ጥያቄዬ ምን መሰላችሁ፡- ነብያትን በተመለከተ የተናገረችው ንግግር ይፈቀዳል? ስማቸው ያረጀ ነው ማለት ይቻላል? ሥማቸው አያምርም ማለትስ ይቻላል? እንዲህ ዓይነቱን ንግግር የተናገረ ሰው ኢማኑ አደጋ አይጋረጥበትም?


መልስ፡- በነብያት እና በሷሊሖች- ከማንም በላይ ደግሞ በሶሓቦች- ስም መጠራት ኃይማኖታዊ ጥቅም አለው። ምርጥ ሥም የነርሱ ስም ነው። አላህ ለምርጥ ባሮቹ የመረጠው ሥም ነው። በነርሱ ስም መጠራት እነርሱን ያስታውሳል። እነርሱን እንድንከተልም ይገፋፋል። ስለዚህ በሸሪዐው በነርሱ ስም መጠራት ተወዳጅ ነው። በሐዲስ እንዲህ የሚል ተዘግቧል፡-

تسموا بأسماء الأنبياء  

“በነብያት ስም ተጠሩ።” አቡዳዉድ እና አቡ የዕላ ዘግበውታል።

በነብያት ስም መጥራት የጠላ ሰው ተሳስቷል። የነብዩን (ሰ.ዐ.ወ) አስተምህሮንም ነቅፏል።

ኢብኑል-ቀዪም “ቱሕፈቱል-መውሉድ ቢአሕካሚል-መውሉድ” የተሰኘው መፅሐፋቸው ላይ እንዲህ ይላሉ፡- “ሰዒድ ኢብኑል-ሙሰይ-ዪብ እንዲህ ብለዋል፡- አላህ ዘንድ ምርጡ ሥም የነብያት ስም ነው።” “ታሪኽ” በተሰኘው በኢብኑ አቢ ኸይሰማ ፅሑፍ ላይ እንደተዘገበው፡- “አቡጦልሓ አስር ልጆች ነበሩት። ሁሉም የሚጠሩት በነብያት ሥም ነው። ዙበይር አስር ልጆች ነበሩት። ሁሉም በሸሂዶች ስም ነው የሚጠሩት። ከዚያም አቡ ጦልሓ ‘እኔ ልጆቼን በነብያት ስም ስጠራቸው አንተ ግን በሸሂዶች ስም ትጠራቸዋለህ?’ አለው። ዙበይርም ‘ልጆቼ ሸሂዶች እንዲሆኑ ስለምመኝ ነው። አንተ ግን ልጆችህ ነብያት እንዲሆኑ አትከጅልም!’ አለው።”

ሙስሊም ላይ የተዘገበ የአቡሙሳ ሐዲስ አለ። እንዲህ ይላሉ፡- “ወንድ ልጅ ተወለደልኝ። ከዚያም ወደ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) አመጣሁት። እርሳቸውም ሙሐመድ አሉት። በተምርም ተሕኒክ አደረጉለት።

ተሕኒክ ማለት፡- ህፃን ልጅ ገና እንደተወለደ ተምርን በሷሊሕ ሰው ምራቅ በሚገባ አላምጠው ካላሙት በኋላ ምላሱን እና ድዱን በመለቅለቅ ወደ ሆዱ የሚገባው የመጀመሪያው ነገር እርሱ እንዲሆን ማድረግ ነው።

ቡኻሪይ “በነብያት ስም ስለመጠራት” የሚናገረው ምዕራፍ ላይ የነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ልጅ ኢብራሂም ተብሎ መጠራቱን እንደ መረጃ ያቀርባሉ።

ሸይኽ ሙሐመድ ሙኽታር አሽ-ሺንቂጢይ “ሸርሑ ዛዲል-ሙስተንቀዕ” ላይ እንዲህ ይላሉ፡- “ልጆችን በሷሊሖች ስም መጥራት ይወደዳል። ይህ በሙጊራ ኢብኑ ሹዕባ ሐዲስ ላይ ተመልክቷል። ሐዲሱ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል ይላል፡- ‘ከናንተ በፊት የነበሩት ህዝቦች ልጆቻቸውን በነብያቶቻቸው እና በሷሊሖቻቸው ስም ይጠሩ ነበር።’ ጥበቡም ግልፅ ነው። ህፃኑ ወጣት ሲሆን፣ የተጠራበትን ነብይ ታሪክ ሲያውቅ ወይም የሷሊሑን ሰው ታሪክ ሲያጠና ወይም የዓሊሙን ህይወት ሲያውቅ ተፅዕኖ ይፈጥርበትና ፈለግ አድርጎ ሊይዘው ይችላል።… ስለዚህ ልጁ ላይ መልካም ስሜት እንዲፈጠር ያደርገዋል። ሥሙም የመልካም ነገር መነሻ ይሆነዋል። ተቃራኒ የሆኑት ስሞችም እንደዚሁ አሉታዊ ተፅዕኖ መፍጠራቸው የማይቀር ነው። ልጆችን በመጥፎና በመናጢ ሰዎች ስም መሰየምም ልጆችን ወደነርሱ ጠባይ ሊስብ ይችላል። ልጆችን በከኃዲያን ስም መጥራት ደግሞ ሐራም ነው። ምክንያቱም እነርሱን መመሳሰል ተከልክለናል።”…

ነገርግን የሚያሳዝነው ሙስሊሞች ላይ ተፅዕኖ እየፈጠረ ያለው የምዕራቡ ዓለም የአስተሳሰብ ጫና አንዳንዶች ከምዕራቡ የሚመጡ ስሞችን ለልጆቻቸው መጠሪያነት እንዲመርጡ አድርጓቸዋል። ሸሪዐዊ ስሞች የሙስሊም ልጆች ጌጥ ነው። ከእምነታቸው ባዳ የሆኑ ስያሜዎች ማንነታቸውን አይወክሉም።

ሸሪዐዊ ስሞችን የማይወድ ሰው ተሳስቷል። አላህን ምህረት መለመን እና ወደርሱ መመለስ ይገባዋል። ውዱን ነብይ ሙሐመድን (ሰ.ዐ.ወ) እወዳለሁ እያለ ስሙን አልወድም ማለት ከራስ ጋር መጋጨት ነው። አንድን ሰው የወደደ ስሙንም ይወዳል። የልጁ መጠሪያ እንዲሆንለትም ይመኛል። ተግባር ደግሞ የልብን ፍቅር ፍንትው አድርጎ ያሳያል። ንግግር ብቻውን ሙግት ነው እንጂ ፍቅርን አያረጋግጥም።

ይሁንና ጠያቂያችን ንግግሯን የጠቀሰልንን ሴት በመልካም እንጠረጥራለን። የምትናገረውን በደንብ አላሰበችበትም ብለን እናስባለን። እንደዚያም ለማለት ፈልጋ ነው ብለን አናስብም። ነገርግን ንግግሯን ታርም። “ዘመናዊ” ሥም ከፈለገች የፈለገችው ስም ከዲን ጋር እስካልተጋጨ ድረስ ልጆቿን ትጥራበት። ነገርግን የነብያትን ስም አልወድም ማለት የለባትም። ሙስሊሞች ዘንድ ውድ የሆነውን ስም ግን አትንካ።

ደግሞም እነዚህ ሥሞች “ዘመናዊ” አይደሉም ማለት ሀሰት ነው። የዐለም ሙስሊሞችን ተጨባጭ ያለማወቅም ምልክት ነው። ጥናቶች እንደሚጠቁሙት በአሁኑ ወቅት በብዛት ደረጃ ከማንም ስም በላይ የሆነው ስም ሙሐመድ ነው።

አላህ የበለጠ ያውቃል!