ለይለቱል ቀድር

Home የፈትዋ ገጽ ዒባዳ ጾምና ኢዕቲካፍ ለይለቱል ቀድር

ጥያቄያለሁበት ለሊት ለይለቱል ቀድር መሆኑን እንዴት ማወቅ እችላለሁ? ይህን የተከበረ ለሊት እንዴትስ ላሳልፍ? ሶላት በመስገድ ወይስ ቁርአን በመቅራት?


መልስ፡ ቢስሚላሂ ረህማኒ ረሒም

ለይለቱል ቀድርን (የውሳኔዋን ለሊት) ህያው ማድረግ እንደሚወደድ የሚጠቁሙ ብዙ ሐዲሶች ተዘግበዋል። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ይላሉ፡-

من قام رمضان إيمانًا واحتسابًا غفر له ما تقدم من ذنبه “ ”ومن قام ليلة القدر إيمانًا واحتسابًا غفر له ما تقدم من ذنبه

“(የአላህን ቃልኪዳን) እያመነና (ምንዳውን) እየተሳሰበ በረመዳን ለሊት የቆመ (የሰገደበት) ሰው ያሳለፈውን ወንጀል በሙሉ ይማራል።” “(የአላህን ቃልኪዳን) እያመነና (ምንዳውን) እየተሳሰበ ለይለቱል ቀድርን የቆመ (የሰገደበት) ሰው ያሳለፈውን ወንጀል በሙሉ ይማራል።” (ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)

ለይለቱል ቀድር የተባረከ ለሊት ነው። አላህ ወህይ (ራእይ) ለማውረድ መርጦታል። አላህ እንዲህ ይላል፡-

حم * وَالْكِتَابِ الْمُبِينِ * إِنَّا أَنزَلْنَاهُ فِي لَيْلَةٍ مُّبَارَكَةٍ إِنَّا كُنَّا مُنذِرِينَ
 

“ሐ.መ (ሓ ሚም)፡፡ አብራሪ በኾነው መጽሐፍ እንምላለን፡፡ እኛ (ቁርኣኑን) በተባረከች ሌሊት ውስጥ አወረድነው፡፡ እኛ አስፈራሪዎች ነበርንና፡፡” (አድ-ዱኻን 44፣ 1-3)

አላህ በዚህ አንቀፅ ውስጥ በመፅሀፉ (በቁርአን) ይምላል። በተባረከ ለሊት እንዳወረደውም ይናገራል። ይች ለሊትም ለይለቱል ቀድር ናት።

ለይለቱል ቀድር የተለያዩ ምልክቶች አሏት። በርሷ ውስጥ ሙስሊሞች የሚጠመዱባቸው የተለያዩ ሥራዎችም አሉ። በዚያ ቀን የሚሠሩ አምልኮዎችም ሌላ ጊዜ ከሚሠሩት ይበልጥ የላቀ ክብርና ደረጃ ያስገኛሉ።

ከለይለቱል ቀድር ምልክቶች መሀል የተወሰኑትን እንጥቀስ። ኢማም ኢብኑ ተይሚያህ ፈታዋ አል-ኩብራ ላይ እንዲህ ይላሉ፡-

“ለይለቱል ቀድር ከረመዳን የመጨረሻው አስር ቀናት ላይ የሚከሠት አንድ ለሊት እንደሆነ ከነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ተነግሯል። ‘ከረመዷን ወር የመጨረሻዎቹ አስር ቀናት ውስጥ ነው ያለችው።’ ብለዋል፤ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)። በአስሩ የረመዷን ወር የመጨረሻ ቀናት በነጠላ የሚቆጠሩት ቀናት ላይ እንደሆነችም የሚጠቁሙ ሐዲሶችም እንዲሁ ተዘግበዋል። ነጠላነት ግን ካለፉት የረመዳን ቀናት ወይም ከሚቀሩት የረመዳን ቀናት አንፃር ሊታይ ይችላል። ስለዚህ ካለፈው አንፃር ካየነው ሀያ አንደኛው፣ ሀያ ሦስተኛው፣ ሀያ አምስተኛው፣ ሀያ ሠባተኛው እና ሀያ ዘጠነኛው ቀን ይበልጥ ለይለቱል ቀድር ሊሆኑ እንሚችሉ ይጠረጠራሉ። እነዚህ ብዙዎች የሚጠብቁበት አቆጣጠር ነው። ይሁንና የቀሩትን የረመዷን ቀናት በማሰብ ልንቆጥርም እንችላለን። ምክንያቱም ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ይላሉ፡-

لتاسعة تبقى لسابعة تبقى لخامسة تبقى لثالثة تبقى

“እርሷ በሚቀሩት ሰባት፣ አምስት፣ ሦስት… ቀናት ውስጥ ትሆናለች።”

በዚህ መሠረት ወሩ ሠላሳ ቀን ከሆነ ከታች ወደ ላይ ሲቆጠር ጥንድ ቀናት የሚሆኑት ለሊቶች ከላይ ወደ ታች ሲቆጠር ለይለቱል ቀድር ሊሆኑ ይችላሉ። ማለትም ሀያ ሁለተኛው ለሊት ዘጠኝ ቀናት የሚቀሩት ለሊት ሊሆን ቻለ። ስለዚህ ሀያ አራተኛው ቀን ደግሞ ሰባት ቀናት የሚቀሩት ለሊት ሆነ… እያልን ልንሄድ ነው። ታላቁ ሶሐባ አቡ ሰዒድ አልኹድሪይ (ረ.ዐ)- በሶሒሕ እንደተዘገበው- ያለፈውን ሐዲስ በዚህ መልኩ ተረድተውታል።

በዚሁ መሠረት ወሩ በሀያ ዘጠኝ ካበቃ ደግሞ ሒሳቡ ከዚህ በፊት ከተጠቆሙት ቀናት ጋር ተመሳሳይ ቀናት ላይ ለይለቱል ቀድርን ልንጠብቅ ነው ማለት ነው። ስለዚህ ሙስሊም ሁሉ የመጨረሻዎቹ አስር ቀናት ውስጥ ለይለቱል ቀድርን በሙሉ ንቃት መጠበቅ ይገባል። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) “አስሩ የመጨረሻ ቀናት ላይ በንቃት ጠብቋት!” ብለዋል። በተለይም የመጨረሻዎቹ ሰባት ቀናት ላይ መጠበቁ በጣም ይጠነክራል። በተለየ ሁኔታ ደግሞ ሀያ ሰባተኛው ለሊት እንደሆነች ኡበይ ኢብኑ ከዕብ (ረ.ዐ) ይነግሩናል። ‘እንዴት አወቁ?’ ተብለው ቢጠየቁ ‘ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) በነገሩን ምልክት ነዋ። የእርሷ (የለይለቱል ቀድር) ንጋት ላይ ፀሀይ ልብስ እንደሚታጠብበት ሳፋ (ጠሽት) ንፁህና ደካማ ሆና ትወጣለች። ሲሉ መልእክተኛው ነግረውናል።’

ኡበይ ኢብኑ ከዕብ ከነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ይዘው የነገሩን ይህ ምልክት የታወቀ የለይለቱል ቀድር ምልክት ነው። ለሊቷ መሀለኛ የአየር ሁኔታ ያላትና ብርሀን ያላት መሆኗ ሌሎች ምልክቶች ናቸው። በእርግጥም አላህ ለአንዳንድ ሠዎች በመናም (በህልም) ሊያሳውቃቸውና ብርሀኗን ሊያሳያቸው ይችላል። ይህ ለይለቱል ቀድር ነው ብሎ የሚነግራቸው ሠው ሊልክባቸው ወይም ልቡን ከፍቶለት እውነት ለይለቱል ቀድር መሆኗን የሚለይበት ነገር ልቡ ውስጥ ሊጥልበት ይችላል።” የኢብኑ ተይሚያህ ንግግር እዚህ ላይ አበቃ።

በእለቱ የሙስሊሞች ሥራ ምን መሆን አለበት?

ለሊቱ የተባረከ ለሊት ነው። ከአንድ ሺህ ወራት በላይ ዋጋ ያለው ለሊትም ነው። አላህ -ልክ ጁምዓ ውስጥ ያለችውን፣ ዱዓ ተቀባይነት የሚያገኝባትን ውድ ሰዓት እና ታላቁን ስሙን (ኢስሙል አዕዘምን) እንደደበቀ ሁሉ- ለይለቱል ቀድርንም ደብቋታል። የመደበቃቸው ምስጢርም ሠዎች እነሱን ለማግኘት እንዲጥሩ ለማድረግ ነው። በእርግጥ ለይለቱል ቀድር መች እንደሆነ በውል ባይታወቅም አስሩ የመጨረሻ ቀናት ውስጥ መሆኑን አሳልፈናል። ስለዚህ እርሷን ለማግኘት አስሩን የመጨረሻ ቀናት ለሊቶች በሙሉ በዚክር፣ በዱዓ፣ ቁርአን በመቅራት፣ ሶላት በመስገድ… ማሳለፍ ያስፈልጋል።

የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) አስሩ የመጨረሻ የረመዳን ቀናት ውስጥ -ከምንም ጊዜው በላይ- ለዒባዳ ይጠነክራሉ። ቁርኣን ያነባሉ። ሶላት ያበዛሉ። ዱዓ ላይ ይጠነክራሉ። ቡኻሪ እና ሙስሊም አዒሻን (ረ.ዐ) ዋቢ በማድረግ እንደዘገቡት:-

أن النبي صلى الله عليه وسلم كان إذا دخل العشر الأواخر أحيا الليل وأيقظ أهله وشد المئزر

“የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) አስሩ የረመዳን የመጨረሻ ቀናት በሚገቡ ጊዜ ለሊቱን ህያው ያደርጋሉ። ቤተሰቦቻቸውን ያነቃሉ። ሽርጣቸውን ያጠብቃሉ።” (ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)

በአህመድና በሙስሊም ዘገባ:-

كان يجتهد في العشر الأواخر ما لا يجتهد في غيرها

“መልእክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) በሌላ ጊዜ ከሚያደርጉት አምልኮ በላቀ ሁኔታ በእነዚህ አስር ቀናት ውስጥ ያደርጋሉ።” (አህመድና ሙስሊም ዘግበውታል)

ለይለቱል ቀድርን እንድንጠብቅ የአላህ ነብይ (ሰ.ዐ.ወ) ብዙ ጊዜ ቅስቀሳዎችን አድርገዋል። ከሰዪዲና አቡሁረይራህ እንደተዘገበው የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡- “(የአላህን ቃልኪዳን) እያመነና (ምንዳውን) እየተሳሰበ ለይለቱል ቀድርን የቆመ (የሰገደበት) ሰው ያሳለፈውን ወንጀል በሙሉ ይማራል።” ስለዚህ ይህ ሐዲስ ለሊቱን በሶላት ማሳለፍ እንሚወደድ እያስተማረ ነው።

ያን ቀን ዱዓ እንድናደርግ የሚቀሰቅሱ ሐዲሶችንም እናገኛለን። ቲርሚዚ አዒሻን (ረ.ዐ) ዋቢ አድርገው ባስተላለፉት ሐዲስ

قلت: يا رسول الله، أرأيت إن علمت أي ليلة ليلة القدر ما أقول فيها؟ قال: قولي: اللهم إنك عفو تحب العفو فاعف عني

“የአላህ መልእክተኛን (ሰ.ዐ.ወ) ለይለቱል ቀድርን ካወኩኝ ምን ብዬ ዱዓ ላድርግ? ብዬ ጠየኩኝ። እርሳቸውም ‘አላህ ሆይ አንተ ይቅር ባይ ነህ። ይቅርታንም ትወዳለህ። ይቅር በለኝ!፤ በይ’ አሉኝ።” (ቲርሚዚ ዘግበውታል)

አላህ የተሻለ ያውቃል!