You are here ታሪክና ስልጣኔ ኢትዮጵያችን የረጅም ጊዜ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ታሪክ ቅኝት (ክፍል 1)

የረጅም ጊዜ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ታሪክ ቅኝት (ክፍል 1)

በሙሀመድ አሊ

ሀገራችን ኢትዮጵያ የ3000 ዓመታት የታሪክ ባለቤት መሆነዋ ይነገርላታል። ነገር ግን ዛሬ ለሃያ አንደኛዉ ክፍለ ዘመን ትዉልድ የሦስት አስርት መቶ ዓመታት ታሪክ ባለቤት ነህ ብለዉ በከንቱ ዉዳሴ ሊደሰኩሩለት እምብዛም አይሻ።

በሰለጠነ አተያይ ስለ አንድ ጽንሠ-ሀሳብ ጥልቅ ምንነት ከመነገሩ በፊት የጽንሰ-ሀሳቡ ትርጉም (defination) ከወገናዊነት (subjective value) እሴት በጠራ መልኩ መቀመጥ አለበት። እንዲሁ በግርድፉ ኢትዮጵያ የ3000 ዓመታት ታሪክ ባለቤት ናት ብሎ መናገሩ አጥጋቢ አይሆንም። በመጀመሪያ የሚከተሉት ነጥቦች/ሀሳቦች ትኩረት ሊቸራቸዉ ይገባል።

1. እዉን ታሪክ ማለት የንጉሶች (Kings) የጄኔራሎች ዜና መዋዕልና ገድል ብቻ ነዉን? ወይስ በአንዲት ሀገር ክብረወሰን ከታህታይ እስከ ላዕላይ መዋቅር የሚኖሩ ማንኛዉም የማህበረሰብ ክፍሎች ሁለንተናዊ የኑሮ ሁኔታ?

2. በራሳቸዉ አመለካከትና ጥቅም የተሸበቡ የህብረተሰብ ክፍሎችን የዉንብድና ዘመን ለተጨቋኙ ታሪክህ ይህ ነዉ በታሪክህ ኩራ ማለቱ አግባብ ነዉን?

3. ጥቂት የማይባሉ የኀብረተሰብ ክፍሎችን ታሪካቸዉንና ማንነታቸዉን አግልሎ፣ ረስቶና አጉድፎ እንዲሁም ዕምነትና ባህላቸዉን ንቆና አጣጥሎ የሚደረገዉ የታሪክ ዘገባ የአንዲት ሀገር ታሪክ ይህ ነዉ ብሎ ለማዉሳት ያስደፍራልን?

4. በጥቅሉ ይህን የመሰለ አካሄድ ለማህበራዊ ኑሮ ደህንነት ለሀገርና ለህዝብ ዕድገት የሚያመጣዉ ዉጤት ምን ይሆን?

5. በልማዳዊ ዕይታ ታሪክ ስላለፈ ክስተት ብቻ (Dry Past) የሚዘክር ነዉ ተብሎ ይወነጀላል። በተጨማሪም ታሪክ ያለፈ ዘመን ዜና መዋዕል፣ ወሬ፣ ተረት፣ ትዉፊት፣ ገድል ነዉ ተብሎም ተገልጧል። ይህ ያረጀ ያፈጀ የታሪክ ግንዛቤ ነዉ። በተለይ በሀገራችን ኢትዮጵያ ለአያሌ ዘመናት ቆይቷል። ይህን መሰሉ የታሪካችን መልክ እስካሁንም አሻራዉ አልጠፋም።

በተቃራኒዉ በትክክለኛዉ መንገድ ዘመናዊ የታሪክ ተመራማሪዎች ታሪክን እንደሚከተለዉ ይገነዘቡታል፣

….ንጉሥ እገሌ ከእገሌ ተወለደ። ከእገሌ ጋር ተዋጋ፤ በጦር ሜዳ ሞተ የሚል ዜና መዋዕል የሚፈየደዉ ነገር የለም። የተወለደ ሁሉ ይሞታል። ይህ ምን አዲስ ነገር አለዉ? እኛ ማስተማር ያለብን ስለነበረዉ ሥርዓት፣ ተቋም፣ ላዕላይ መዋቅር፣ ታህታይ መዋቅር፣ የአስተዳደር ድርጅትና የኢኮኖሚ ሥርዓት ነዉ።.... የታሪክ ትምህርትና እዉቀት ያገርና የኀብረተሰብ ግንባታ መሠረትና መሳሪያ ነዉና። (ላጲሶ፣21)

በተጨማሪም፣

ታሪክ በትርጉሙም በተግባሩም የሰዉ ልጅ ያለፈዉን ዘመን ሥራ በሥፍራና (ቦታ) በጊዜ ከተጨባጭ መረጃ በማጥናትና በማገናዘብ ዛሬ የራሱን ብሎም የኀብረተሰቡን ህልዉና ህይወትና ተግባር የሚያዉቅበት ዕዉቀት፣ የዕዉቀት ስልትና መሳሪያ ነዉ። ያለፈዉ የሰዉ ሥራ መረጃ፣ ሥፍራና (ቦታ) ጊዜ የታሪክ ምንጮች እንጂ በራሳቸዉ ታሪክ፣ ዕዉቀትና ጥበብ አይደሉም። (ላጲሶ፣111)

በጥቅሉ ስለ ታሪክ ግንዛቤ ይህንን ያክል ከተባለ በኢትዮጵያ ለረጅም ዘመናት የእልምናንና የኢትዮጰድያ ሙስሊሞችን ታሪካዊ ትዉስታ ባጭሩ ለመቃኘት እንሞክራለን። በመሠረቱ ኢስላም በኢትዮጵያ አቀባበል ከተደረገለት ጊዜ ጀምሮ ያለዉን ታሪክ በዚህች በአጭር ጽሁፍ ለማሳየት መሞከር “አባይን በጭልፋ” እንደማለት ነዉ።

መጀመሪያ በኢትዮጵያ የእስልምናንና የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን ታሪክ ከማጥናታችን በፊት ዕርምት ሊወሰድባቸዉ የሚገቡ ጉዳዮችን ማጤን አስፈላጊ ነዉ። ይህ ታሪክ ፈፅሞ በኢትዮጵያ ትኩረት ተሠጥቶት አልተጠናም ለማለት ባያስደፍርም የራሱ የሆነ እንቅፋቶች (Limitation) ጎልቶ ይታይበታል። እነዚህ ችግሮች እንደሚከተሉት ናቸዉ።

  • ያለፉት ጥናቶች እስልምናን በኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን ታሪክ ከራሱ አስተያየት (its own perspectives) አንፃር አላጠኑትም፣
  • የእስልምናንና የሙስሊሞችን ታሪክ በኢትዮጵያ ለማጥናት የምንጠቀምባቸዉ የመረጃ ምንጮች የዉጭ የአረብ ፀሐፊዎች ሥራ፣ የአዉሮፓ መንገደኞች (travler account) ዘገባ፣ አልያም የኢትዮጵያ የክርስቲያን ዜና መዋዕል ፀሐፊዎችን ሥራ ነዉ።

ለአንዲት ሀገር ዕድገትና ብልጋግና የሁሉም ዜጎች ታሪክ፣ እምነት፣ ባህልና ወግ በእኩል መጠናት አለበት። የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን ታሪክ ማጥናት ፋይዳዉ ለታሪኩ ባለቤቶች ብቻ ሳይሆን ለሀገሪቱ አያሌ መልካም አስተዋፅኦ ሲያበረክቱ እንደቆዩና ማበርከት እንደሚችሉ ያሳያል።  ሀገራችን ኢትዮጵያ በ7ኛዉ ክፍለ ዘመን ከመካ ቀጥላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሙስሊሞችን ያስተናገደች መሆኗ ይታወቃል። ነገር ግን ከዚሁ ዘመን ጀምሮ ኢስላም ለኢትዮጵያ ባይተዋርና የሥጋት ምንጭ ተደርጎ ተቆጥሮ ቆይቷል። ገና ከጅምሩ የኢስላም ዕጣ ፈንታ መጤ የፖለቲካ ክስተትና ለኢትዮጵያ ህልዉና ስጋት ተደርጎ ተፈርጇል። ይህ አባዜ የተጠናወተዉ ጭፍን አመለካከት ኢስላም ለኢትዮጵያ ባህል መጎልበት የተጫወተዉን ሚና፣ የሙስሊሞችን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ፣ ኢስላም ለሥነጽሑፍ መስፋፋትና መጠናከር ያደረገዉን ዉለታና በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ህዝቦች ኀብረ-ብሄርነት ሂደት ያበረከተዉን መልካም አስተዋፅኦ መካድ ነዉ።

ከ7ኛዉ ክፍለ ዘመን መባቻ በኤደን ባህረ ሠላጤና በምስራቅ አፍሪካ የኢስላም በሠላማዊ መንገድ መስፋፋት በዘመኑ ለነበረዉ የአክሱም ስልጣኔ የራስ ምታት ሆኖበት ነበር። በመሠረቱ በዚህ ክልል ሙሉ የኢስላም መጠነ ሰፊ የስርጭት ሂደት የተከናወነዉ የንግድን እንቅስቃሴ መንገድ በመጠቀም ነበር። የዚህን አካባቢ የኢስላም ስርጭት ስናጠና አንድም የጦርነት ዘገባ አናገኝም። እዉነታዉ ይህ ሆኖ ሳለ በ7ኛዉ ክፍለ ዘመን የአክሱም መንግሥት በቤጃ ጎሳዎች አመፅና በዳሞት ንግሥት (ዮዲት) በተደረገበት ተከታተይ ጥቃት ተዳከመ። ለዚህ የአክሱም የድክመትና የዉድቀት መንስኤ የኢስላም መስፋፋት እንደዋና ምክንያት ተደርጎ ይቆጠራል። ለምሳሌ ማርጋሪ ፐርሃም የአልቨሬስን አባባል እንዲህ በማለት አስቀምጣዋለች፡-

የአክሱም ሃያልነትና ሥልጣኔ ጣሪያ በደረሠበት ጊዜ (በ7ኛዉ ክፍለ ዘመን) የሙስሊሞች ወረራ ለኢትዮጵያ ታላቅ የጥፋት በር ሆኖባታል በዛን ጊዜ የነበረዉ የአክሱምን ሥልጣኔ ለመገመት ቢያስቸግርም ዛሬ የአዉሮፓ ስልጣኔ እደረሠበት ደረጃ ላይ ነበር ማለት ይቻላል። (ፐርሃም)

ይህንንና መሠል መሠረተ ቢስ የታሪክ መረጃ የሌላቸዉ አባባሎች ከዕዉነት የራቁ መሆናቸዉን በመረጃ የሚያሳዩ የታሪክ ምሁሮችም አሉ። ፕሮፌሠር ታደሠ ታምራት (Church and State) በሚለዉ መፅሀፋቸዉ ለአክሱም መዳከምና መንኮታኮት የሙስሊሞች መስፋፋት ነዉ የሚለዉን አተያይ በግልፅ የሚጠቀሱ ታሪካዊ መረጃ እንደሌለ አስቀምጠዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አቢሲኒያዉያን የባህር በርንና የንግድ መስመሮችን ለመቆጣጠር ከአረብ ሙስሊሞች ጋር ፍጥጫዉ ተጋጋለ። በዚህም የተነሣ ኢትዮጵያዊያን በ702 የጅዳን ወደብ ወረሩም፤ መዘበሩም። ለዚህ አፍራሽ ድርጊት የዐረቢያ ሙስሊሞች አፀፋ ምላሽ ለመስጠት ተገፋፍተዉ የዳህላክን ደሴት ተቆጣጠሩ። የዳህላክ ደሴት በሙስሊሞች ስር መዉደቋ ኢስላም በአፍሪካ ቀንድ እንዲስፋፋ ጥርጊያ መንገድ ከፍቷል።

ኢስላም ይህንን ሠላማዊ የመስፋፋት ሂደት ተጠቅሞ በአቢሲኒያ በስፋት ለመሠራጨት ከመቻሉም በላይ በ9ኛዉ ክ/ዘመን መገባደጃ ኢስላማዊ ስርዎ መንግሥት ለመገንባት ችሏል። በ896 የማክዙሚ ስርዎ-መንግሥት በምስራቅ ሸዋ ተቋቋመ። የዚህ ስርዎ መንግሥት መስራችና አስተዳዳሪዎች ዘራቸዉን ከነብዩ ሙሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) ጋር ያያይዛሉ። ይህ የመጀመሪያዉ ኢስላማዊ የሸዋ ሱልጣኔት ከ896-1285 በከፍተኛ የዕድገት ደረጃ ላይ ቆይቷል። ምንም እንኳን በዚህ ሱልጣኔት መሀል የግዛት ዘመን ላይ በ11ኛዉ ክ/ዘመን አጋማሽ የአክሱም መንግሥት ለመጨረሻ ጊዜ ወድቆ በዛጉዬ ቢተካም ለሙስሊሞች እምብዛም እንቅፋት አልፈጠረም ነበር። እንዲያዉም በአንፃሩ ለኢትዮጵያ ሙስሊሞች የሠላምና መረጋጋት ዘመን መሆኑ ይዘከራል። በኢትዮጵያ ታሪክ ዉስጥ አብዛኛዉን ጊዜ የሙስሊሞች ታሪክ በሀገሪቱ ፖለቲካና መንግሥት መቀያየር ሁኔ ላይ የተንጠለጠለ ነዉ። አንድ መንግሥት ተቀይሮ የሀገሪቱን የሥልጣን መንበር ሲይዝ የሙስሊሞች ሁኔታ በፊተኛዉ ከነበረዉ የከፋ ወይም ተቀራኒ ይሆናል። ስለዚህም ነዉ ኢስላም የሀበሻን ምድር ከረገጠበት ጊዜ ጀምሮ ዳግም የሰለሞናዊ ስርዎ መንግሥት የተመሠረተበት ጊዜ (1270) ድረስ በአንፃሩ የእፎይታና የሠላም ዘመን ያሳለፈዉ። ዳሩ ግን በ1270 የአገዉ ስርዎ መንግሥት ወድቆ በዳግም ሠለሞናዊያን ሲተካ የኢስላምና የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ታሪክ በኢትዮጵያ መልኩን ቀይሯል።

 

Share this post

ተያያዥ ርዕሶች

Comments  

 
+1 #1 sualih 2014-11-10 20:13
ማሻአላህ
Quote
 

Add comment


Security code
Refresh