በጉንፋን እና በብርድ ወቅት ያስነጠሰን ማስደሰት

Home የፈትዋ ገጽ ማህበራዊ ጉዳዮች በጉንፋን እና በብርድ ወቅት ያስነጠሰን ማስደሰት

ጥያቄ፡- አሰላሙአለይኩም ወራህመቱላሂ ወበረካቱሁ። ባጠገቤ እጅግ ብዙ ጊዜ የሚያስነጥስ ባልደረባ አለኝ። በጣም በተከታታይ ያስነጥሳል። (የርሐሙከሏህ) ማለት አለብኝ? ወይስ አስነጥሶ ሲጨርስ ለሁሉም አንድ ጊዜ ልበለው? አመሰግናለሁ።


መልስ፡- አንድ ሰው በሚያስነጥ ጊዜ “አልሐምዱሊላህ” ወይም “አል-ሐምዱሊላህ ዐላ ኩሊ ሐል” ወይም “አልሐምዱሊላሂ ረቢል ዓለሚን” ማለት ይወደድለታል። ይህ በሐዲስ የተዘገበ ነው። ዑለሞች በሙሉ ይህንን ማለት ተወዳጅ እንደሆነ ያምናሉ።

አሏህን ሲያመሰግን የሰማው ሰው ደግሞ እርሱን ማስደሰት ደግሞ ተገቢው ነው። ማስደሰት ማለት “አሏህ ይዘንልህ” (የርሐሙከሏህ) ማለት ነው። ይህም በሐዲስ ውስጥ በግልፅ የተዘገበ ነው። ሐዲሱን ዐዒሻ ናቸው ያስተላለፉት እንዲህ ይላሉ፡-

إذا عطس أحدكم فليقل: الحمد لله، وليقل من عنده: يرحمك الله: وهذا من حق المسلم على المسلم.

“አንዳችሁ ካስነጠሰ ‘አልሐምዱሊላህ’ ይበል። አጠገቡ ያለም ሰው ‘የርሐሙከሏህ’ ይበለው። ይህ ሙስሊም በሙስሊም ላይ ያለው ሐቅ ነው።”

ነገርግን ማስነጠሱ ከሦስት በላይ ሲሆን አሏህ ጤና እንዲሰጠው ዱዓ ያደርግለታል እንጂ አያስደስተውም። ምክንያቱም ኢማም ማሊክ፣ ከዐብዱሏህ ቢን አቢበክር አባታቸውን ዋቢ በማድረግ እንደዘገቡት የአሏህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡-

إِنْ عَطَسَ فَشَمِّتْهُ ثُمَّ إِنْ عَطَسَ فَشَمِّتْهُ ، ثُمَّ إِنْ عَطَسَ فَشَمِّتْهُ ، ثُمَّ إِنْ عَطَسَ فَقُلْ : إِنَّكَ مَضْنُوكٌ

“አንዴ ካስነጠሰ አስደስተው፤ ከዚያም ደግሞ ካስነጠሰ አስደስተው። ከዚያም በድጋሚ ካስነጠሰ ታመሃል በለው።”

ከሰለማ ቢን አል-አክወዕ እንደተዘገበው የአሏህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡-

يُشَمَّتُ الْعَاطِسُ ثَلَاثًا ، فَمَا زَادَ فَهُوَ مَزْكُومٌ . رواه ابن ماجة

“ሦስት ጊዜ ያስነጠሰ ሰው ያስደስቱታል። ከዚያ ከጨመረ ግን ህመምተኛ ነው።” ኢብኑ ማጃህ ዘግበውታል።

ነወዊይ (አሏህ ይዘንላቸው) እንዲህ ይላሉ፡- “ማስነጠሱ ከተደጋገመ እና ከተከታተለ ሱናው ሦስት እስከሚሞላ ድረስ እርሱን ማስደሰት ነው። ኢማም ሙስሊም፣ አቡዳዉድ እና ቲርሙዚይ ከሰለማ ቢን አል-አክወዕ እንዲህ የሚል ተዘግቧል፡- “የአሏህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ባጠገባቸው አንድ ሰው አስነጠሰ፤ እርሳቸውም “የርሐሙኩሏህ” አሉት። ከዚያም ደግሞ አስነጠሰ የአሏህ መልእክተኛም (ሰ.ዐ.ወ) “ሰውየው ታሟል” አሉ።” እነዚህ ሙስሊም ዘገባውን ያሰፈረባቸው ቃላት ናቸው።”

አሏህ የተሻለ ያውቃል!