የልጅ ልጆችን በስጦታ እኩል ማድረግ

Home የፈትዋ ገጽ ቤተሰብ የልጅ ልጆችን በስጦታ እኩል ማድረግ

ጥያቄ፡- አባቴ መኪና አለው። እናም መኪና ስላልነበረኝ ለአራት አመታት ለኔ ትቶልኝ እጠቀምበት ነበር። ከስድስት ወር በፊት አላህ ልጅ ሰጠኝና በአባቴ ስም ሰየምኩት። አባቴም መኪናው ለልጄ ስጦታ እንዲሆን መወሰኑን ተናገረ። ጥያቄዬ ምን መሰላችሁ? እኔ አምስት ወንድሞች አሉኝ። ሦስቱ ከኔ በፊት አግብተዋል። ሁሉም ልጆች ወልደዋል፤ አልሐምዱሊላህ። ልጆቻቸውንም በአባቴ ስም ነው የጠሯቸው። ነገርግን አባቴ ለማናቸውም ስጦታ አልሰጠም። ይህ ስጦታ ይፈቀዳል?


መልስ፡- አያት ልክ ለልጆቹ ፍትሀዊና እኩል መሆን እንዳለበት ለልጅ ልጆቹም እንደዚያው ፍትሀዊና እኩል መሆን አለበት። ኢማም ነወዊይ እንዲህ ብለዋል፡- “እናት ለልጆቿ ስጦታ ከሰጠች እንደ አባት ልጆቿን በእኩል የስጦታዋ ተካፋይ እንዲሆኑ ማድረግ አለባት። አያትም እንዲሁ ነው።” (ረውደቱጥ-ጧሊቢን ቅፅ 5፣ ገፅ 397)

አል-ሀይሰሚይ ቱሕፈቱል-ሙሕታጅ፣ ቅፅ 6፣ ገፅ 307 ላይ እንዲህ ብለዋል፡- “ወላጅ- አባት ወይም እናት እያለ ወደላይ ቢወጣም- ለልጆቻቸው እና ለልጅ ልጆቻቸው- ስጦታ ሲሰጡ ሁሉንም እኩል ማድረግ ይወደድላቸዋል። ይህ ሃሳብ ይህንን ብይን ለልጆች በሚሰጥ ስጦታ ላይ ብቻ ከገደቡት ሰዎች ሃሳብ ጋር ይቃረናል። ስጦታው የአክብሮት ስጦታም ሆነ ምፅዋት ወይም ሌላ መልክ ያለው ስጦታ ቢሆንም ብይኑ አይለይም። ያለ ምክንያት ሁሉንም እኩል ካላደረገ አብዝሃኞቹ ዑለሞች ዘንድ የሚጠላ ድርጊት ፈፅሟል። ሐራም ሰርቷል ያሉ ብዙ ዑለሞችም አሉ። የዚህ ብይን መረጃ የቡኻሪይ ሐዲስ ነው። እንዲህ ይላል፡-

اتقوا الله واعدلوا بين أولادكم

“አላህን ፍሩ፤ ለልጆቻችሁም ፍትሀዊ ሁኑ።”

አል-መርዳዊይ “አል-ኢንሷፍ” የተሰኘው መፅሐፋቸው ቅፅ 7፣ ገፅ 137 ላይ እንዲህ ብለዋል፡- “ለልጆቻችሁ በምትሰጡት ስጦታ ላይ ሁሉንም እኩል አድርጉ ሲባል የልጅ ልጆችንም ያካትታል። ይህ የመዝሀባችን ሁነኛው አቋም ነው።”

ስለዚህ ተገቢው ነገር ለልጅህ የተሰጠውን ስጦታ መመለስ ነው። ለወላጅ አባትህም ጉዳዩን እና የሸሪዐውን ብይን አስረዳው። ምክንያቱም የአባትህ ድርጊት ወንድሞችህን ሊያስከፋ ይችላል። ለማይረባ የዱንያ ጥቅም ደግሞ ወንድሞችህን ለምን ታጣለህ? አባትህስ ከወንድሞችህ ጋር ለምን ይቀያየማል?

ደግሞም ስጦታው ለህፃኑ አይመስልም። በእርግጥም ስጦታው ላንተ ይመስላል። የምትጠቀምበት አንተ ነህ የምትሆነው። ህፃኑ አይደለም። ስለዚህ ወላጅህ ከወንድሞችህ አንተን እያበለጠህ ይመስላል። ይህ ደግሞ እንደገለፅነው በግልፅ- በተረጋገጠ የሐዲስ ዘገባ- የተከለከለ ድርጊት ነው።

አላህ የበለጠ ያውቃል!