ዕቃው በሽያጭ ላይ እያለ ጉድለት ተገኘበት

Home የፈትዋ ገጽ ማህበራዊ ጉዳዮች ዕቃው በሽያጭ ላይ እያለ ጉድለት ተገኘበት

ጥያቄ፡- ነጋዴ ወይም ሻጭ የዕቃውን ጉድለት ለገዢው መግለፅ ግዴታ አለበት? ለገዢው ጉድለቱን ከተናገረ ግን ሊከስር ይችላልና ምን ያድርግ?


መልስ፡- ሻጭ ለገዢው እቃው ላይ ያለውን ነውር የመበየን ግዴታ አለበት። ነውሩን መደበቅ ማታለል ነው። ማጭበርበር እና ማምታትም ነው። ይህ ደግሞ ያለጥርጥር ሐራም ነው።

የኢብኑ ማጀህ “ሱነን” ላይ እንደተዘገበው የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ይላሉ፡-

المسلم أخو المسلم لا يحل لمسلم باع من أخيه مبيعاً وفيه عيب إلا بيّنه

“ሙስሊም የሙስሊም ወንድም ነው። ሙስሊም ለወንድሙ ሲሸጥ ዕቃው ነውር ካለበት ጉድለቱን መግለፅ ግዴታው ነው።”

የኢማም አሕመድ “ሙስነድ” ላይ እንደተዘገበው የአላህ ነብይ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ይላሉ፡-

لا يحل لأحد أن يبيع شيئاً إلا بيّن ما فيه، ولا يحل لأحد يعلم ذلك إلا بيّنه

“ማንኛውም ሰው ምንም ነገር ሲሸጥ በዕቃው ላይ ያለውን ጉድለት ሳይነግር መሸጥ አይፈቀድለትም። ማንም ሰው ቢሆን ይህንን ነውር ካወቀ መበየን ግዴታው ነው።”

የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ምግብ ከሚሸጥ ሰው አጠገብ አለፉ። ስንዴ ነበር የሚሸጠው። ከዚያም እጃቸውን ወደውስጥ ሰደዱ። እጃቸውም እርጥበት አገኘ። ከዚያም እንዲህ አሉ፡-

يا صاحب الطعام ما هذا ؟

“የእህል ባለቤት ሆይ! ይህ ምንድን ነው!?” አሉት።

ሰውየውም “ዝናብ ነክቶት ነው!” አለ።

እርሳቸውም፡-

هلاّ جعلته ظاهراً حتى يراه الناس من غش فليس منا

“እና ግልፅ አታደርገውም ሰዎች እንዲያዩት! ያታለለ ከእኛ አይደለም!” አሉ።

የእቃን ጉድለት መበየን እያንዳንዱ ሙስሊም እና ነዋሪ ሊከተለው የሚገባ የወንድም መብት (ሐቅ) ነው። ይህ ተግባር የበረካ እና የብልፅግና መንገድ ነው። ገንዘብን ያበዛል፤ መልካም ሲሳይን ይባርካል። በሶሒሕ ሐዲስ እንዲህ የሚል ተዘግቧል፡-

والبيعان – أي المتبايعان – إن صدقا وبيّنا بورك لهما في بيعهما، وإن كذبا وكتما محقت بركة بيعهما

“ሻጭና ገዢ… እውነት ከተናገሩና ነውርን ከገለፁ ግብይታቸው ላይ በረከት ይደረግላቸዋል። ከዋሹና ከደበቁ ግን የግብይታቸው በረከት ይጠፋል።”

ማታለል የዕቃን ነውር በመደበቅ እንደሚሆነው ሁሉ መጥፎውን በጥሩው በመቀላቀልም ሊደረግ ይችላል። መጥፎውን ከጥሩው ጋር ቀላቅሎ በአንድ ላይ መሸጥ ማታለል ነው። የእቃውን መደበኛ ተመን ከማያውቅ ሰው ደብቆ መሸጥም ማታለል ነው። በቁጥር፣ ሚዛን እና ስፍርን ማጓደልም ማታለል ነው፤ ክዳት ነው።

በጥቅሉ ማታለል በማንኛውም መልኩ፣ በማንኛውም ዘዴ ክዳት ነው፤ ክፋት ነው። አላህ ደግሞ ከዳተኞችን አይወድም።

አላህ ሆይ መልካም ሲሳይ፣ ሐላል የሆነ ሪዝቅ እንለምንሃለን። እኛንም ሆነ ወንድሞቻችንን የምንደጋገፍ፣ የምንመካከር እና እውነተኞች እንድታደርገን እንለምንሃለን! አሚን!

ወላሁ አዕለም!