ኩረጃ


ጥያቄ፡- የትምህርት ቤት ፈተና ቢከብደኝ ከክፍል ባልደረቦቼ ብቀስም (ብኮርጅ) ወንጀል ይሆንብኛል? አብዛኛውን የትምህርቴን መፅሃፍ በሚገባ አጥንቼ ነበር። ነገር ግን አንዳንድ ምዕራፎችን በትኩረት ሳላጠና አልፌያቸው ነበር። ነገር ግን ፈተናው ካጠናሁት ምዕራፍ ሳይሆን ካላጠናሁት ሆነብኝና መውደቅ ፈራሁ። እባከችሁን ፈትዋ ስጡኝ?


መልስ፡- ቢስሚላሂረህማን አር-ረሂም። ፈተና ውስጥ ማጭበርበር /መኮረጅም ብትለው/ የማህበረሰባችንን ህልውና ከሚፈታኑ ጉዳዮች አንዱ ነው። እንዲህ አይነት ቅጥፈት የተሠራጨበት ማህበረሰብ አንገቱን ቀና ሊያደርግና ማንነቱ ሊጠራ አይችልም። በዚህ መሠል ቅጥፈት ብቁ ያልሆኑ ሠዎች የሥልጣን ማማን ይቆናጠጣሉ። የማህበረሰቡ የእድገት መስመርም ህቡዕ በሆኑ አመራሮች ይሠናከላል።

ገና ከመገንባታቸው የሚሰነጣጠቁ ህንፃዎች፣ የአሠራር መዝረክረክና መንዛዛት፣ የባለጉዳዮች እንግልት እና ሌሎችም ማህበረሰብን የሚፈታተኑ የእድገት ፀር ይህ -ማጭበርበር ነው። ንግድ ቦታም ይሁን ትምህርት ቤት፣ ሆስፒታልም ሆነ መንግስት መስሪያ ቤት ማጭበርበር ሀራም ነው። ፈተና መክበድ ሃራምን ለመስራት ምክንያት አይሆንም።

ሼክ ዓጠያ ሶቀር (የአዝሃር ኢስላማዊ ዩንቨርስቲ የቀድሞ የፈትዋ ኮሚቴ አባል) መሠል ለሆኑ ጥያቄዎች የሠጡትን ምላሽ እነሆ፡- “ማታለል በማንኛውም ጉዳይ ቢሆን ሃራም ነው። ነብያዊ ሀዲስም የሚጠቁመን ይህንኑ ነው።

من غشنا فليس منا

“ያታለለን ከኛ አይደለም!” (ሙስሊም ዘግበውታል።)

ይህ ብይን እውነትን ስለሚጋፋ ወይም ማታለል ስለሚባል ሁሉ የተሰጠ አጠቃላይ ብይን ነው። የሚያታልል ሃጢያት ፈጽሟል። አታላይን የሚተባበርም የወንጀሉ ተጋሪ ነው። የፈተና መክበድ ማታለልን የሚያስፈቅድ ምክንያት አይሆንም። ፈተና ያስፈለገው በርትቶ የሚያጠና ተማሪን ከአላጋጩ ለመለየት ነው። ኢስላምም ለሁለቱ እኩል ቦታ አይሰጥም።”

የሁለቱን አኩል መሆንም ጤነኛ አእምሮ አይቀበለውም። አሏህ እንዲህ ይላል፡-

أَمْ نَجْعَلُ الَّذِينَ آمَنُوا وَعَمِلُوا الصَّالِحَاتِ كَالْمُفْسِدِينَ فِي الْأَرْضِ أَمْ نَجْعَلُ الْمُتَّقِينَ كَالْفُجَّارِ

“በእውነቱ እነዚያን ያመኑትንና መልካሞችን የሠሩትን በምድር ውስጥ እንደሚያጠፉት እናደርጋለን? ወይስ አላህን ፊረዎቹን እንደ ከሓዲዎቹ እናደርጋለን?” (ሷድ 38፤28)

ፈተና በተለይ የዕውቀት ሠዎችን የምናበላልጥበት ቁልፍ ነው። አሏህ እንዲህ ይላል፡-

قُلْ هَلْ يَسْتَوِي الَّذِينَ يَعْلَمُونَ وَالَّذِينَ لَا يَعْلَمُونَ

“እነዚያ የሚያውቁና እነዚያ የማያውቁ ይስተካከላሉን?” (አዝ-ዙመር 39፤9)

በፈተና ውስጥም ይሁን በሌሎች ጉዳዮች ላይ ማታለል ማህበረሰቡን የሚያናውጥ ከባድ አደጋ ነው። ምክንያቱም ውሸትን ያበለጽጋል። እውነት ያደበዝዛል። እንግዲህ በተዛባ ሚዛን ብቁ ያልሆኑ ሠዎች ከፍ ባለ ሚዛን ተመዝነው የማይገባቸውን ክብር እያገኙ በሚኖሩበት ሁኔታ ማህበረሰብ ፍትህ አያገኝም። ኩረጃ አማና ማፍረስ ነው። በዚህም ምክንያት ከቂያማ ትንሳኤ መድረስ ምልክቶች አንዱ ነው። ጥያቄውን እንደመለስን ተስፋ እናደርጋለን።

አላህ (ሱ.ወ) የተሻለ ያውቃል።