ኢፍጣርና የመግሪብ ሶላት፤ የቱን ላስቀድም?

Home የፈትዋ ገጽ ዒባዳ ጾምና ኢዕቲካፍ ኢፍጣርና የመግሪብ ሶላት፤ የቱን ላስቀድም?

ጥያቄ፡- የቱን እናስቀድም? ኢፍጣርን ወይስ የመግሪብን ሶላት?  ፀሀይ ከጠለቀች በኋላ ከመግሪብ ሶላት በፊት ትንሽ በመቅመስ ጾምን መፍታት ይበቃል ወይስ ሙሉ ምግብ መመገብ ይቻላል?


መልስ፡- ቢስሚላሂር-ረሕማኒር-ረሒም አል-ሐምዱሊል-ላሂ ረብ-ቢል ዓለሚን ወስ-ሶላት ወስ-ሰላም ዐላ ረሱሊላህ

የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) በእሸት ተምርና በደረቅ ተምር ያፈጥሩ እንደነበር ተዘግቧል። ይህን ካላገኙ ግን በውሃ ያፈጥሩም ነበር። ጸሀይ መጥለቋን እንዳረጋገጡ ፊጥራቸውን ያቻኩሉ ነበር። ፊጥርን ሰዎች እንዲያፈጥኑም ይቀሰቅሱ ነበር። ከዚያም መግሪብን ይሰግዱና ፊጥራቸውን ያሟላሉ።

ከሶላት በፊት ፊጥሩን ማሟላት የሚያስገድደው ምክንያት ከተፈጠረ ግን ችግር የለውም። አሟልቶ ያፍጥርና ይስገድ። ጾመኛው ለምግቡ የጓጓ ከሆነ ግን ከሶላት በፊት ፊጥሩን ቢያሟላው የተወደደ ይሆናል።

በአል-አዝሀር ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶክተር ሙሐመድ ሰይድ አሕመድ አል-መሲር እንዲህ ይላሉ፡-

የአላህ መልእክተኛን ከምንከተልባቸው መልካም ስርዐቶች መሀል አንዱ ነው፤ ጸሀይ መጥለቋ እንደተረጋገጠ በፍጥነት ማፍጠር። ቲርሙዚይ እና ነሳኢይ ከአነስ እንደዘገቡት እንዲህ ብለዋል፡- “የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ከሶላት በፊት በጥቂት የተምር እሸቶች ያፈጥሩ ነበር። እሸት ካጡ ግን በተምር ያፈጥሩ ነበር። ተምርም ካጡ በጥቂቱ ውሃን ይጎነጩ ነበር።” ያፈጥሩበት የነበረው ተምር ሦስት ፍሬ እንደነበርም ተዘግቧል።

ይህ ነብያዊ ስርዐት ጥበብ አለው። ምክንያቱም ሰውየው የዕለት ጾሙን ሲያገባድድ በረሀብና በጥም ውስጥ ሆኖ የመግሪብን ሶላት መስገዱ ተገቢ አይደለም። በተጨማሪም ለዕለቱ ጾም የተመደበው ጊዜ መገባደዱን እንዲያውቅ ያደርገዋል። ከጾም በመውጣትም አላህ ጾሙን ለማገባደድ ስላበቃውም እንዲደሰት ያደርገዋል። ከጾም መውጣት የሚችለው ደግሞ ተከልክሎ የነበረውን ምግብ በመቅመስ ነው።

ፊጥርን ማስቸኮል ተወዳጅ ነው። ነገርግን ጥቂት በመቅመስም ቢሆን ሱናው ይገኛል። በጥቂት ተምሮች፣ በጉንጭ ውሃ… ወይም በሌላ። ከዚያም ሰውየው የመግሪብን ሶላት ይስገድና አስከትሎ ሙሉ ማዕዱን ይመገባል።

ነገርግን ሰውየው ምግብ ካስፈለገው እና በዚህ ምክንያት ሶላቱን አሳምሮ መስገድ የሚሳነው ከሆነ ፊጥሩን አሟልቶ ከጨረሰ በኋላ መስገድ ይችላል። እንደውም በእንዲህ አይነት ሁኔታ ላይ ላለ ሰው የተሻለው ይህ መንገድ ነው።

ይህ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) ቡኻሪና ሙስሊም በዘገቡት ሐዲሳቸው ላይ የገለጹት ነው፡-

إذا قرُب العشاء وحضرت الصلاة فابدأوا به قبل أن تصلوا صلاة المغرب ولا تعجلوا عن عشائكم 

“እራት ከቀረበ እና ሶላት ከተጣደችባቹ ከመግሪብ ሶላት በፊት በእራት ጀምሩ። ከእራታችሁም አትጣደፉ።” 

እመቤታችን ዓኢሻ ከአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንደዘገቡት እንዲህ ብለዋል፡-

لا صلاةَ بحضرة الطعام 

“ምግብ ከተጣደ (ከቀረበ) ሶላት የለም።”