ሽልማት የሚያስገኙ ኩፖኖችን እና የሎተሪ እድል ሸሪዓዊ ብይን

Home የፈትዋ ገጽ ማህበራዊ ጉዳዮች ሽልማት የሚያስገኙ ኩፖኖችን እና የሎተሪ እድል ሸሪዓዊ ብይን

ጥያቄ፡- አሰላሙዐለይኩም ወራህመቱላህ ወበረካቱሁ። የስፖርት ውድድሮች፣ ትምህርታዊ ውድድሮች፣ የጠቅላላ ዕውቀት ውድድሮች ሽልማት ሸሪዓዊ ብይን ምን እንደሆነ እንድታሳውቁኝ እፈልጋለሁ። በተጨማሪም የተለያዩ ካምፓኒዎች የሚያወጧቸው ሽልማት የሚያስገኙ ኩፖኖች እና ሎተሪዎች ይፈቀዳሉ?


መልስ፡- ቢስሚላሂር-ረሕማኒር-ረሒም። አልሐምዱሊላሂ ረቢል-ዐለሚን። ወስ-ሶላት ወስ-ሰላም ዓላ ረሱሊላህ ወበዕድ፡-

የተለያዩ የውድድር ሽማቶች አሉ። ሁሉም ዓይነት ሽልማት የራሱ የሆነ ሸሪዓዊ ብይንም አለው። የሚከተሉት የተለመዱ የሽልማት ዓይነቶች ናቸው።

አንደኛ፡- ከሁለቱም ወገን ገንዘብ ተዋጥቶ የሚደረግ የውድድር ሽልማት

ሁለቱም ወገን የተወሰነ የገንዘብ መጠን ያዋጡና ይወዳደራሉ ወይም ይጫወታሉ። ከዚያም አሸናፊው የሁሉንም ገንዘብ ይወስዳል። በዚህ መሠረት አንዱ ቡድን አሸናፊ ሆኖ ገንዘቡን ሲታደል ሌላኛው ግን ባለዕዳ ሆኖ ገንዘቡን ይበላል። ይህ ዓይነቱ ውድድር ከሸሪዓው አንፃር ቁማር ነው፤ ሐራም ነው። ምክንያቱም መዋጮው ከሁለቱም በኩል የወጣ በመሆኑ ያለ አግባብ የሰውን ገንዘብ ከመብያ መንገዶች አንዱ ተደርጎ ነው የሚወሰደው። የአሏህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ይህንን ከልክለዋል። እንዲህ ይላሉ፡-

من لعب بالنرد فقد عصى الله ورسوله (رواه أحمد) 

“በየጠርዛቸው ከአንድ እስከ ስድስት ነጠብጣብ ባላቸው ትናንሽ የመጫወቻ ክቦች (የነጠብጣብ ቁማር/ Dice) የተጫወተ ሰው አሏህና መልእክተኛውን አመፀ።” አሕመድ ዘግበውታል።

ሁለተኛው፡- ከሦስተኛ ወገን በሚገኝ ገንዘብ ለመሸለም የሚደረግ ውድድር ነው

በውድድሩ ውስጥ የማይሳተፍ ሦስተኛ ሰው የተወሰኑ ገንዘቦችን ያስይዛል። ከዚያም የተያዘው ገንዘብ ለአሸናፊው ይሠጣል። ገንዘቡን የሚያስይዘው ተወዳዳሪዎችን ለማበረታታት ነው። ይህ አይነቱ ሽልማት የሚፈቀድ ነው። ነገርግን ጨዋታው ወይም ውድድሩ ሸሪዓው ከፈቀዳቸው ጨዋታዎች መሀል የሚመደብ እና ከሸሪዓው ዓላማ ጋር የማይጋጭ መሆን አለበት።

ሦስተኛው፡- ከገለልተኛ ወገን የሚመደቡ የውድድር ሽልማቶች

አንዳንዴ ገለልተኛ የሆኑ ተቋማት- ለምሳሌ፡- መንግስት፣ ድርጅቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ትምህርታዊ ወይም የበጎ አድራጎት ተቋማት፣ ማህበረሰባዊ ተቋማት እና መሰል ድርጅቶች ለአሸናፊዎች ሽልማቶችን ያዘጋጃሉ። ለምሳሌ፡- የቁርኣን ውድድሮች ላሸነፉ ሰዎች የሚሰጡ ሽልማቶችን ያዘጋጃሉ። የጥናታዊ ፅሁፎችን፣ የበጎ ሥራ ውድድሮችን እና የመሳሰሉትን አወዳድረው ይሸልማሉ። ይህ አይነቱ ሽልማት በሸሪዓው ይፈቀዳል። እንደሚፈቀድ የሚጠቁም ሸሪዓዊ ማስረጃም አለ። የአሏህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ይላሉ፡-

لا سبق إلا في نصل أو خف أو حاضر (رواه أبو داود)

“በጦር ውርወራ፣ በግመል ወይም በፈረስ እንጂ ውድድር የለም።” አቡዳዉድ ዘግበውታል።

ይህ ገንዘብ ለሽልማት የሚመደብበት ምክንያት ተወዳዳሪዎችን ለማነሳሳት፣ ለበጎ ነገሮች እንዲበረታቱ ለማድረግ፣ ሰዎችንም ለዚህ ተግባር ለመገፋፋት መሆን አለበት። “ወደ መልካም ነገር ያመላከተ ሰው መልካሙን ነገር እንደሰራው ሰው ይቆጠራል።”

አራተኛው፡- ከተለያዩ ካምፓኒዎች እቃ ሲገዛ የሚሰጥ ኩፖን ላይ የተመሰረተ ሽልማት ነው

ይህ ሰዎች አንድን እቃ እንዲገዙ ለማድረግ ከሚጠቅሙ የገበያ ማሻሻጫ ዘዴዎች መሀል አንዱ ተደርጎ ይወሰዳል። ካምፓኒዎቹ የተወሰነ ገንዘብ በመመደብ ሽልማት ያዘጋጃሉ። ከዚያም እጣ በማውጣት እጣ የወጣለትን ኩፖን ይሸልማሉ። እንዲህ ዓይነቱ የሽልማት አይነት እንዴት ነው? በሸሪዓው ይፈቀዳል ወይ? ነው የተጠየቅነው ጥያቄ…

ዑለሞች በዚህ ጉዳይ ላይ የተለያዩ አቋሞች ነው ያላቸው እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡-

  • አንዱ ቡድን ሐራም ነው ብሎ ያምናል። ምክንያቱም ይህ ሽልማት የተመረኮዘው እድል ላይ ነው። ሰው ሳይሰራና ሳይለፋ ገንዘብ እያገኘ በመሆኑ መከልከል አለበት ይላሉ።
  • ሌላኛው ቡድን ግን ይህ ሽልማት ከድርጅቶቹ እንደሚሰጡ ስጦታዎች መታየት አለባቸው ይላል። የሰዎችን ገንዘብ ያለምንም አስተዋፅዖ በብላሽ እንደመብላት መታሰብ የለበትም የሚል ሃሳብ አለው።
  • ሦስተኛው የፉቀሃዎቹ ቡድን ደግሞ የሚከተለውን ይላል፡-
  1. የሚሸጠው እቃ ዋጋ ውስጥ የሽልማት ኩፖኑ ዋጋ ከተካተተ ቁማር ይመስላል። ምክንያቱም ገዢዎችን ከዋጋው ጭማሪ በማስከፈል ነው የሽልማቱን ገንዘብ የሰበሰቡት። ስለዚህ ያልተሸለሙት ገዢዎች የሽልማቱን እዳ ተሸክመዋል። ይህ ደግሞ ቁማር ነው።
  2. በሽልማቱ ምክንያት የሸቀጡ ዋጋ ተፅዕኖ ላይ ካልወደቀ ሽልማቱ ከድርጅቱ ለገዢዎቹ የተሰጠ እድል ወይም ስጦታ ተብሎ ሊታሰብ ይችላል። በመሆኑም እንደ ሸሪዓ የሚያስከለክለው ምክንያት አይኖርም።

አምስተኛው፡- የሎተሪ ቲኬቶችን በመግዛት የሚገኝ ሽልማት ነው

የፊቅህ ልሂቃን በሙሉ የሎተሪ ቲኬቶችን መቁረጥ ሐራም እንደሆነ ይስማማሉ። በመሆኑም የቲኬቱ ዋጋ ተጣርቶ ለበጎ ሥራ የሚውል ቢሆንም እንኳን የሚያስፈቅደው ምንም ምክንያት አይኖርም። ምክንያቱም ይህ ከሸሪዓ አንፃር የተከለከለ ቁማር ነው። በእድል ላይ የተመሰረተ የሰዎችን ገንዘብ ያለ አግባብ- በብላሽ- ከመብላት ጎራ የሚቆጠር ሥራ ነው። አሏህ በቁርዓኑ ከልክሎታል።

يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا إِنَّمَا الْخَمْرُ وَالْمَيْسِرُ وَالْأَنصَابُ وَالْأَزْلَامُ رِجْسٌ مِّنْ عَمَلِ الشَّيْطَانِ فَاجْتَنِبُوهُ لَعَلَّكُمْ تُفْلِحُونَ

“እናንተ ያመናችሁ ሆይ! የሚያሰክር መጠጥ ቁማርም ጣዖታትም አዝላምም ከሰይጣን ሥራ የኾኑ እርኩስ ብቻ ናቸው። (እርኩስን) ራቁትም ልትድኑ ይከጀላልና።” (አል-ማኢዳ 5፤ 90)

አሏህ የተሻለ ያውቃል!