ስንት ረከዓ እንደሰገድኩ ተምታታብኝ

Home የፈትዋ ገጽ ሰላት ስንት ረከዓ እንደሰገድኩ ተምታታብኝ

ጥያቄ:- አንድ ለሰላት የቆመ ሰው ሦስት ይሁን አራት ስንት ረከዓ እንደሰገደ እርግጠኛ መሆን ካልቻለና ከተጠራጠረ ምን ማድረግ ይኖርበታል?


መልስ፡- የሸሪዓ ህግ የሚለው በጥርጣሬ ጊዜ አንድ ሰው እርግጠኛ የሆነበትን አሊያም ወደ እርግጠኛነት የቀረበበትን ነው መከተል ያለበት። በሰሂህ ሙስሊም እንደተዘገበው የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዐለይህ ወሠለም እንዲህ ብለዋል:- “ከናንተ መካከል አንዳችሁ በሰላቱ የተጠራጠረ እንደሆነ ሦስት ይስገድ አለያም አራት በርግጠኝነት ካለወቀ ጥርጣሬውን ይተውና እርግጠኛ የሆነበትን ይከተል። ከዚያም ከማሰላመቱ በፊት ሁለት ሱጁድ ያድርግ። አምስት ሰግዶ ከሆነ ሁለቱ ሱጁዶች ሰላቱን ሙሉ ያደርጉለታል። አራት ሰግዶ የሆነ እንደሆነ ደግሞ እኚህ ሱጁዶች ሸይጧንን ለሀፍረት ይዳርጋሉ።” (ሙስሊም)

በሌላ የቡኻሪ ሀዲስ ደግሞ አንድ ሰው በሰላቱ የተጠራጠረ እንደሆነ ሊሆን ይችላል ያለውንና በጣም የመሠለውን ያድርግ። ከዚያም በመጨረሻው ላይ ሁለት ሱጁድ አስ-ሰህው (የመርሣት ሱጁድ) ያድርግ የሚል ተጠቅሷል።

ስለሆነም አንድ ሰው ሦስት አሊያም አራት ረከዓ ስንት እንደሰገደ ከተጠራጠረ ሆኖም ግን ሦስት በመስገዱ ላይ እርግጠኛ መሆን ቢችልም ሆነ ቢጠራጠር ጥርጣሬውን ወደኋላ በመጣል አንድ ረከዓ ጨምሮ አራት ይሙላና በመጨረሻም ሶላቱን በተስሊም ከማገባደዱ በፊት ሱጁድ አስ-ሰህው (ሁለቱ የመርሳት ሱጁዶችን) ያድርግ። ይህ የሻፊዒያ መዝሀብ መንገድ ሲሆን በጥንቃቄውና በመረጃ የተሻለው ነው። አላህ የተሻለ ያውቃል!