ሱሑር በጾም ላይ የሚፈጥረው ተጽዕኖ

Home የፈትዋ ገጽ ዒባዳ ጾምና ኢዕቲካፍ ሱሑር በጾም ላይ የሚፈጥረው ተጽዕኖ

ጥያቄ፡- ሱሑር መመገብ ግዴታ ነው? “ሱሑር ተመገቡ። ሱሑር መመገብ ውስጥ በረከት አለ።” የሚለው ሐዲስ ውስጥ በረክት/በረካ ማለት ምን ማለት ነው?


መልስ፡- ቢስሚላሂር-ረሕማኒር-ረሒም አል-ሐምዱሊል-ላሂ ረብ-ቢል ዓለሚን ወስ-ሶላት ወስ-ሰላም ዐላ ረሱሊላህ

ሱሑር ሱና ነው እንጂ ግዴታ አይደለም። ግዴታው ሰውየው በለሊት ከንጋት በፊት ኒያ አድርጎ ማደሩ ብቻ ነው። ኒያ በየዕለቱ መሆን አለበት ወይስ ለሙሉው ወር አንድ ኒያ ይበቃል የሚለው ላይ የዑለሞች ልዩነት እንዳለው ሆኖ።

የሳዑዲው ዓሊም ሸይኽ ኢብኑ ጂብሪን እንዲህ ይላሉ፡-

ሱሑር መመገብ ሱና ነው። ተወዳጅ ተግባር ነው። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) እንዲህ ይላሉ፡-

تسحروا فإن في السحور بركة

“ሱሑር ተመገቡ፤ በሱሑር ውስጥ በረከት አለ።” (ቡኻሪና ሙሰሊም)

“ሱሑር ተመገቡ።” የሚለው ትዕዛዝ ቀና መንገድ  የመጠቆሚያ (ኢርሻድ) ትዕዛዝ ነው። ግዴታነትን የሚያስገነዝብ ትዕዛዝ አይደለም። ለዚህ ነው ምክንያቱን አብረው የነገሩን። ሱሑር የሚበላው በረከት ፍለጋ ነው። በረከት ማለት ብዙ መልካም ነገር ማለት ነው።

የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ሱሑር ሳይበሉ እንደቀሩ ተዘግቧል። ምክንያቱም እርሳቸው ጾመው ውለው ምንም ሳይቀምሱ ቀጣዩን ቀን በማስከተል ጾመዋል። ስለዚህ ሱሑር መመገብ ግዴታ እንዳልሆነ በተግባር አሳይተውናል። ሱሑር ተወዳጅ ሱና እንደሆነ የሚጠቁሙ ሐዲሶች ብዙ ናቸው። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ይላሉ፡-

فصل ما بين صيامنا وصيام أهل الكتاب أكلة السحر

“በእኛና በመፅሐፍቱ ባለቤቶች ጾም መሀል ያለው ልዩነት ሱሑር መመገብ ነው።” (ሙሰሊም)

የአላህ  መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ባልደረቦቻውን ሱሑር እንዲበሉ አዘዋቸዋል። በተምር ወይም በአንድ ጉንጭ ወተትም ቢሆን እንኳን ሱሑር ብሉ ብለዋቸዋል።

በሐዲሱ ውስጥ “በረከት” ሲባል ሱሑር የሚበላ ሰው ሥራው በረከት ይኖረዋል ማለት ነው። በዚያን ቀን በጎ ስራዎች እንዲሰራ አላህ ያግዘዋል። ጾም አይከብደውም። ሶላት ከመስገድ አያሳንፈውም። ከዚክሮች እና በመልካም ከማዘዝና ከመጥፎ ነገሮች ከመከልከል አያቅበውም። ሱሑር መብላት የተወ ሰው ግን ጾም ከበጎ ስራዎች ያካብደዋል። ድካሙ ለእንቅልፍ እና ለስንፍና ይዳርገዋል።

ወላሁ አዕለም!