መንገደኛ መቼ ነው የሚያፈጥረው?

Home የፈትዋ ገጽ ዒባዳ ጾምና ኢዕቲካፍ መንገደኛ መቼ ነው የሚያፈጥረው?

ጥያቄ፡- ሰውየው ጉዞ ለመውጣት ከወሰነ በኋላ መቼ ነው ማፍጠር የሚፈቀድለት?


መልስ፡- ቢስሚላሂር-ረሕማኒር-ረሒም አል-ሐምዱሊል-ላሂ ረብ-ቢል ዓለሚን ወስ-ሶላት ወስ-ሰላም ዐላ ረሱሊላህ

ሰማንያ አምስት ኪሎ ሜትር እና ከዚያ በላይ የሚጓዝ መንገደኛ በረመዷን የማፍጠር ፍቃድ አለው። ነገርግን በሌላ ጊዜ ያፈጠረውን ያካክሳል። በመንገደኛ ሰው ላይ የተገደቡ ህግጋት የሚጀምሩት መቼ ነው በሚለው ሃሳብ ዙሪያ ዑለሞች የተለያየ ሀሳብ ሰንዝረዋል። የተሻለው ሃሳብ- ወላሁ አዕለም- የጉዞ ህጎች የሚጀምሩት ሰውየው የሚነሳበትን ሃገር፣ ከተማ ወይም መንደር ሲያልፍ ነው። ለምሳሌ ከአዲስ አበባ የሚነሳ የአዲስ አበባ ነዋሪ አዲስ አበባን ካለፈ ጀምሮ ነው የመንገደኛ ህጎች የሚጀምሩት። ከአዲስ አበባ ከመውጣቱ በፊት ማፍጠር አይችልም። ምክንያቱም ሰውየው ሃሳቡን እንዲቀይር የሚያደርግ ጉዳይ ገጥሞት ጉዞውን ሊተወው ይችላል። ስለዚህ ሰበቡ ሳይገኝ በፊት ፍቃዱን መተግበር የለበትም። ተጓዥ መሆኑ የሚረጋገጠው ከመኖሪያ ቀዬው ሲወጣ ብቻ ነው።

በአል-አዝሃር ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶክተር ዐብዱረህማን አል-ዐደዊይ እንዲህ ይላሉ፡-

አላህ እንዲህ ይላል፡-

وَمَن كَانَ مَرِيضًا أَوْ عَلَىٰ سَفَرٍ فَعِدَّةٌ مِّنْ أَيَّامٍ أُخَرَ يُرِيدُ اللَّهُ بِكُمُ الْيُسْرَ وَلَا يُرِيدُ بِكُمُ الْعُسْرَ

“በሽተኛ ወይም በጉዞ ላይ የኾነም ሰው ከሌሎች ቀኖች ቁጥሮችን (በልኩ) መጾም አለበት። አላህ በእናንተ ገሩን (ነገር) ይሻል። በእናንተም ችግሩን አይሻም።” (አል-በቀራ 2፤ 185)

አላህ ለሙሳፊር ጾም የመፍታት ፍቃድ ሰጥቷል። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) እንዲህ ይላሉ፡-

إن الله وضع عن المسافر الصوم

“አላህ ለሙሳፊር ጾምን ትቶታል።”

በጉዞ ወቅት ማፍጠር ይፈቀዳል። ነገርግን መጾም የማያስቸግረው ሰው ከሆነ መጾሙ ይበልጣል። ሐምዛ አል-አስለሚይ፡- “የአላህ መልእክተኛ ሆይ በጉዞ ወቅት የመጾም አቅም አለኝ። ብጾም ችግር አለው?”  አሉ። የአላህ መልእክተኛም “ይህ የአላህ ፍቃድ ነው። እርሱን ከያዘ መልካም ነው። መጾም የፈለገም ኃጢያት የለበትም።” ሙስሊም ዘግበውታል።

በጉዞ ወቅት ማፍጠር የሚፈቀደው ሶላት ማሳጠር የሚፈቀድበትን ርቀት ያህል ለሚጓዝ ሰው ነው። ይህም- እንደብዙ ዑለሞች ግምት- ሰማንያ አምስት ኪሎሜትር ያህል ይሆናል። የሚኖርበትን ቀዬ ካለቀቀ ሰውየው ተጓዥ ነው ተብሎ አይታሰብም። ጉዞ ለመውጣት የወሰነ ሰው በተግባር የመኖሪያ ቀዬውን ክልል እስካላለፈ ድረስ ተጓዥ አይባልም። ስለዚህ ክልሉን ከማለፉ በፊት ማፍጠር አይችልም።

ሰውየው በጉዞ ወቅት ችግር የሚያገኘው ከሆነ ወይም የጉዞውን ድካም የሚጨምርበት ከሆነ ማፍጠር የተመረጠ ይሆናል። ጃቢር በዘገቡት ሐዲስ “የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ከዛፍ ስር ወድቆ ሰዎች ውሃ የሚያፈሱበትን ሰው ተመለከቱና ‘ምን ሆኖ ነው?’ አሉ። ‘የአላህ መልእክተኛ ሆይ ጾመኛ ነው።’ አሏቸው። የአላህ መልእክተኛም፡-

ليس من البر الصيام في السفر

በጉዞ ወቅት መጾም መልካም አይደለም’።”

ተጓዡ ለጂሃድ (ለትግል) የዘመተ ከሆነ ማፍጠር የተሻለ ይሆናለታል። መጾም ይጠላበታል። ጉዳቱ በጨመረ ቁጥርም መጠላቱም ይጨምራል። ጾም በውጊያ ወቅት የሚያዳክመው ከሆነም ይጠላል።

አንዳንድ ዑለሞች ዘንድ ከፈጅር በኋላ- በቀኑ መጀመሪያ ወይም በቀኑ መካከል- ጉዞ ከጀመረ የማፍጠር ፍቃድ አይኖረውም ብለው ያምናሉ። ነገርግን- በጠቀስነው መልኩ መንገደኛ እስከሆነ ድረስ- ማፍጠር ይፈቀድለታል። ምክንያቱም ጉዞ ከንጋት በፊት ከተገኘና በቀኑ ወቅትም ከቀጠለ ማፍጠር ማስፈቀዱ አያጨቃጭቅም። ስለዚህ በቀኑ መካከል ወይም በቀኑ መጀመሪያ ላይ ከፈጅር በኋላ ሲከሰትም ፍቃድ ያስገኛል። ልክ እንደህመም ማለት ነው። በለሊትም ሆነ በቀኑ መካከል ከተከሰተ ጾም መፍታት ያስፈቅዳል። ሁለቱ በአንድነት በቁርኣን የተገለፁ ጾም መፍታት የሚያስፈቅዱ ሰበቦች እስከሆኑ ድረስ ተነጣጥለው አይታዩም።

መንገደኛ በጉዞው ወቅት ያፈጠረውን ቀዷ ማውጣት አለበት።

ወላሁ አዕለም!