ሒጃብ በኢስላም


ጥያቄ:- በእሰልምና ዉስጥ የሒጃብ ድንጋጌ ምንድነው?


መልስ:- ሒጃብ ለአካለመጠን በደረሠች ሙስሊም ሴት ላይ ሁሉ ግዴታ ነው። ይህም ሴት ልጅ ሐይድ የምታይበት ዕድሜ ነው። ድንጋጌውም በቁርኣን፣ በሐዲሥና በዑለሞች ስምምነት የፀና ነው። አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል:-

يَا أَيُّهَا النَّبِيُّ قُل لِّأَزْوَاجِكَ وَبَنَاتِكَ وَنِسَاءِ الْمُؤْمِنِينَ يُدْنِينَ عَلَيْهِنَّ مِن جَلَابِيبِهِنَّ ذَٰلِكَ أَدْنَىٰ أَن يُعْرَفْنَ فَلَا يُؤْذَيْنَ

“አንተ ነቢዩ ሆይ! ለሚስቶችህ፣ ለሴቶች ልጆችህም፣ ለምእምናን ሚስቶችም ከመከናነቢያዎቻቸው በላያቸው ላይ እንዲለቁ ንገራቸው። ይህ እንዲታወቁና (በባለጌዎች) እንዳይደፈሩ ለመኾን በጣም የቀረበ ነው።” (አል-አሕዛብ 33፤59)

وَقُل لِّلْمُؤْمِنَاتِ يَغْضُضْنَ مِنْ أَبْصَارِهِنَّ وَيَحْفَظْنَ فُرُوجَهُنَّ وَلَا يُبْدِينَ زِينَتَهُنَّ إِلَّا مَا ظَهَرَ مِنْهَا وَلْيَضْرِبْنَ بِخُمُرِهِنَّ عَلَىٰ جُيُوبِهِنَّ

“ለምእምናትም ንገራቸው፡- ዓይኖቻቸውን ይከልክሉ። ብልቶቻቸውንም ይጠብቁ። ጌጣቸውንም ከእርሷ ግልጽ ከኾነው በስተቀር አይግለጡ። ጉፍታዎቻቸውንም በአንገትጌዎቻቸው ላይ ያጣፉ።” (አን-ኑር 24፤ 31)። ጉፍታ ሲባል ራስን የሚሸፍነው ነው።
በሐዲሥም የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ):-

يَا أَسْمَاءُ إِنَّ الْمَرْأَةَ إِذَا بَلَغَتِ الْمَحِيضَ لَمْ يَصْلُحْ أَنْ يُرَى مِنْهَا إِلَّا هَذَا وَهَذَا، وَأَشَارَ إِلَى وَجْهِهِ وَكَفَّيْهِ

“አስማእ ሆይ! ሴት ልጅ ለወር አበባ የደረሠች እንደሆነ ከዚህ እና ከዚህ ዉጭ ማሳየት አይፈቀድላትም።” ብለዋታል። ወደ ፊታቸውና መዳፎቻቸው በማሳየት። (አቡ ዳዉድ ዘግበውታል)

ከነሳኢ ዉጭ ስድስቱ የሐዲሥ ዘጋቢዎች እንዳስተላለፉት የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ):-

لَا يَقْبَلُ اللَّهُ صَلَاةَ حَائِضٍ – من بلغت سن المحيض- إِلَّا بِخِمَارٍ

“ለሐይድ የደረሠችን ሶላት አላህ ያለ ጉፍታ አይቀበልም።” ብለዋል።
የሙስሊሙ ኡማ – የጥንቶቹም ይሁኑ የኋለኞቹ በሒጃብ ግዴታነት ላይ ሙሉ ስምምነት አሳይተዋል። በየትኛውም ሙስሊም አማኝ ዘንድ የሒጃብ ግዴታነት የሚታወቅ እውነታ ነው (አል-ማዕሉሙ ሚነዲኒ ቢዶሩራ)። ሒጃብ ሙስሊሙን ሙስሊም ካልሆነው ለመለየት የምንጠቀምበት መገለጫ ብቻ አይደለም፤ ኢስላማዊ ግዴታ ነው።